ኢትዮጵያና ቤልጂየም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2004 (ዋኢማ) – ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ከቤልጂየም ጋር በቅርበት እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ አስታወቁ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጽህፈት ቤታቸው የቤልጂየም የመከላከያ ሚኒስትር ሚስተር ፒተር ዲ ክሬምን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ በአካባቢያዊ ሰላምና ፀጥታ ዙሪያ ከቤልጂየም ጋር ለመሥራት ዝግጁ ናት፡፡

ቤልጂየም በአውሮፓ ኅብረት አባልነቷ በዚህ በኩል ከፍተኛ ሚና ትጫወታለች የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ኃይለማሪያም ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንድን ከግጭትና ከቀውስ የፀዳ ክፍለ አህጉራዊ ቀጣና ለማድረግ ቤልጂየምን ጨምሮ ዓለም አቀፋዊ ትብብር ማጠናከር እንደሚገባም ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

ሚስተር ክሬም በበኩላቸው ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የልማት ባለሥልጣን(ኢጋድ)ና በአፍሪካ ኅብረት የላቀ ሚና ያላት አገር እንደመሆኗ መጠን፤ ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላለች ብለዋል፡፡

ከዚህ አንጻር አገራቸው የአካባቢውን ሰላምና መረጋጋት በተለይ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሰራ አረጋግጠዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አማካሪ አቶ አራጋው ጥላሁን ከውይይቱ በኋላ እንደገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ለሚኒስትሩ በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሁኔታ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋቸዋል፡፡

ቤልጂየም የአውሮፓ ኅብረት መሥራች አገር ስትሆን፤ መዲናዋ ብራስልስ ደግሞ የኅብረቱና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን አገሮች ድርጅት ( ኔቶ)ዋና መቀመጫ ነው፡፡

የአገሪቷ ሕዝብ ብዛት 11 ሚሊዮን ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ጋር የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡