ከማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ የወጪ ንግድ ከ137 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 8/2004/ዋኢማ/ – ሀገሪቱ በግማሽ የበጀት ዓመቱ ከማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ የወጪ ንግድ ብቻ ከ137 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ የተገኘው 137 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ከቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ከአግሮ ፕሮሰሲንግና ከኬሚካልና ፋርማስዩቲካል ምርቶችን ወደተለያዩ የዓለም ሀገራት በመላክ ነው።

በአጠቃላይ  በግማሽ የበጀት ዓመቱ 202 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 137 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር የተገኘ ሲሆን፤ ይህም የእቅዱን 68 በመቶ አፈፃፀም ያሳያል ብለዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 80 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር ጋር ሲነፃፀር የ70 በመቶ እድገት ማሳየቱንም አቶ መላኩ አስታውቀዋል።

ከዘርፉ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 471 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት የታቀደ ሲሆን፤ እቅዱን ለማሳካትም ለኤክስፖርቱ አስተዋፅኦ በሚያደርጉ ዘርፎች ላይ የድጋፍና የክትትል ስርዓትን ዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘርፉ በግማሽ የበጀት ዓመቱ ገዥ ኩባንያዎች የሚያቀርቡት የገበያ ትዕዛዝ በተወሰኑ ወቅቶች የመቀያየር ባህሪ፣ አዳዲስና ዘላቂ የገበያ ትዕዛዝ አግኝተው አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ጊዜ መውሰድና ሌሎች ችግሮች በኤክስፖርቱ እቅድ አፈፃፀም ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ  አቶ መላኩ ገልፀዋል።