አየር መንገዱ አምስት ኪው 400 ኔክስትጄን የተባሉ አውሮፕላኖችን ገዛ

አዲስ አበባ፤  የካቲት 10 ቀን 2004 (ዋኢማ) – የኢትዮጵያ አየር መንገድ አምስት ኪው 400 ኔክስትጄን የተባሉ አውሮፕላኖችን ለመግዛት የሚያስችለውን ስምምነት ትናንት ተፈራረመ።

አየር መንገዱ ዛሬ ለኢ ዜ አ እንደገለጸው ነዳጅ ቆጣቢ የሆኑትን አውሮፕላኖች ለመግዛት የሚያበቃውን ስምምነት ከቦምባርዲየር ኤሮስፔስ ኩባንያ ጋር ተፈራርሟል።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ”ኪው 400 ኔክስጄን አውሮፕላኖች በቁጠባ፣በሥራ አፈጻጸምና መንገደኞችን ለማስተናገድ የምናደርገውን ጥረት ያሳካሉናል” ብለዋል።

አውሮፕላኖቹ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት የተቀላጠፈና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችሉም ገልጸዋል።

የቦምባርዲየር ኩባንያ ፕሬዚዳንት ማርክ አርካሞን በበኩላቸው ኩባንያው በአፍሪካ ኪው 400ና ኪው 400 ኔክስጄን የተባሉ 40 አውሮፕላኖችን ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለሌሎች አየር መንገዶች መሸጡን አስታውቀዋል።

አውሮፕላኖቹ በሰሜን አፍሪካ በረሃዎችም ከሰሃራ በስተ ደቡብ ባሉት የአፍሪካ አገሮች ተፈትነው ብቃታቸውን እያስመሰከሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አየር መንገዱ ለአዲስ አበባ ቅርበት ባላቸውና ወደ አጎራባች አገሮች በሚያደርጋቸው የበረራ መሥመሮቹ ኪው 400 የተባሉትን አውሮፕላኖች ይጠቀማል።

አዲስ የገዛቸው ኪው 400 ኔክስትጄን አውሮፕላኖች የኢትዮጵያን የንግድና የቱሪዝም ገበያ ለማሳደግ ያስችላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክቷል።

ኪው 400 ኔክስትጄን አውሮፕላን ከነዳጅ ቆጣቢነታቸው በተጨማሪ የአየር ብክለትን በመቀነስም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው መግለጫው ያስረዳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 48 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፣ከመካከላቸውም ስምንቱ ኪው 400 የተባሉት ናቸው።አሁን ግዢያቸው የተፈጸሙት ሞዴሎች የኪው 400 አውሮፕላኖቹን ብዛት 13 ያደርሳቸዋል።

አየር መንገዱ አምስት አህጉሮችን የሚያካልሉ 64 የበረራ መሥመሮች እንዳሉት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዘገባው አስታውሷል።