የደቡብ ክልል ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ጉባዔ ተጀመረ

ሐዋሳ፤ የካቲት 19/2004 (ዋኢማ)– በደቡብ ክልል በግማሽ በጀት ዓመቱ የክልሉን ብሎም የአገሪቱን ልማት የሚያፋጥኑ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ፤ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት አራተኛ ዙር አራተኛ መደበኛ ጉባዔ ዛሬ ተጀምሯል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የክልሉን የ2004 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ አመት የእቅድ አፈፃፀም ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የክልሉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ባለፉት ስድስት ወራት መላውን አርሶ አደርና በየደረጃው የሚገኘውን አስፈፃሚ አካል በልማት ስራዎች ላይ ማሳተፍ ተችሏል።

በ2003/2004 ምርት ዘመን በሁሉም ደረጃ በተደረገ ርብርብ በክልሉ የተሻለ ምርት መመዝገቡን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንኑ ተሞክሮ በቀጣይ ምርት ዘመን በመተግበር የክልሉን ብሎም የአገሪቱን ልማት ለማፋጠን ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።

የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና እንክብካቤ እንዲሁም የመስኖ እርሻን የማስፋፋት ሥራ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ሽፈራው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማሳካት በየዘርፉና በየእርከኑ ዝርዝር እቅዶች ተዘጋጅተዋል፤ በእቅዱ ላይም ግልፅነት የመፍጠር ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

የልማታዊ ሰራዊት አደረጃጀቶችን በማጠናከር መላውን አርሶ አደር የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የክልሉን የተፈጥሮ ሃብት ለመጠበቅና ለመንከባከብ ከጥር ወር ጀምሮ በ118 ወረዳዎችና 2ሺ 877 ቀበሌዎች በየዕለቱ በአማካይ 2 ነጥብ 78 ሚሊየን ህዝብ በተፋሰስ ልማት ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ እስካሁን በሕዝብ ተሳትፎ ከ226 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የጉልበት አስተዋፅኦ መገኘቱንም ተናግረዋል።

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለፃ በከተሞች የመሬት አቅርቦትና አስተዳደር ከኪራይ ሰብሳቢነትና ከመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፀዳ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅትና ክለሳ በመጠናቀቅ ላይ ነው።

በከተሞች ፈታኝ የሆነውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ተግባራት ለመከላከል ከነዋሪው ጋር ውይይት መካሄዱን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ከከተማ አስተዳደር ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች መገምገማቸውንና የሕዝቡን ሃብት በመዘበሩ ላይ የሥነ-ምግባርና ፀረ-0 ሙስና ኮሚሽን ክስ መመስረቱን ተናግረዋል።

በንግድ ዘርፍ የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራት ለማስወገድ በተደረገው ግምገማ አስር አመራሮች ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል።

እንደ አቶ ሽፈራው ማብራሪያ 128 ባለሙያዎችም ወደ ሌላ ዘርፍ እንዲዘዋወሩ የተደረገ ሲሆን፤ 23 ሰራተኞች በህግ እንዲጠየቁ፣ 80 ደግሞ በመንግስት ሰራተኞች አስተዳደር ደንብ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተደርጓል።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ገነት ወልዴ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቶች የሕዝብ ተሳትፎ ማረጋገጫ ተቋማት እንደመሆናቸው የምክር ቤት አባላት የወከላቸውን ህዝብ የልማትና የዴሞክራሲ ተሳትፎ ማጎልበት እንዳለባቸው ጉባዔውን ሲከፍቱ አሳስበዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆየው 4ኛ መደበኛ ጉባዔ በዘጠኝ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።

የዳኞችና የካቢኔ አባላት ሹመት፣ የተጓደሉ የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ማሟላትና የአንድ የምክር ቤቱ አባል ያለመከሰስ መብት ጉዳይ ለምክር ቤቱ ከቀረቡ አጀንዳዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።