በኢትዮጵያ የጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመምና ቅባት እህሎችን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ የ6ካቲት 20/2004 (ዋኢማ) – በኢትዮጵያ የጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመምና ቅባት እህሎች ምርት በ2007 ዓ.ም በእጥፍ እንደሚያድግ ይጠበቃል ሲል ንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ይህንን ለማሳካትም የግሉን ዘርፍ ማበረታታትን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የንግድ ሚኒስትሩ ከበደ ጫኔ ተናገረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በኢትዮጵያ የጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመምና ቅባት እህል ላኪዎች ማህበርና በንግድ ሚኒስቴር ትብብር የተዘጋጀውን የመጀመሪያው አለም አቀፍ የጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመምና የቅባት እህሎች ጉባዔ ሲከፍቱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመምና ቅባት እህል ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኃይሌ በርሄ በበኩላቸው የመንግስትን ጥረት በማገዝ የግሉ ዘርፍም የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም የጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመምና ቅባት እህሎችን ምርት ለማሳደግ እና በተቀናጀ መልኩ አቀነባብሮ ለገበያ ለማቅረብ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡

“ኢትዮጵያ የተለያዩ አዝዕርቶች መገኛ” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው ጉባዔ የኢትዮጵያ ምርቶች በአለም ገበያ ላይ በስፋት እንዲገቡ ለማስቻል አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

ከአውሮፓ፣ ከእስያና ከአፍሪካ የተውጣጡ በርካታ ገዢ ሀገራትና በዘርፉ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ተወካዮች የጉባዔው ተሳታፊዎች መሆናቸውን ኢሬቴድ ዘግቧል፡፡