በአማራ ክልል ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ቱሪስቶች ታሪካዊና የተፈጥሮ የመስህብ ስፍራዎችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2004(ዋኢማ) – በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን የሚጎበኙ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ባህል፣ቱሪዝምና ፓርኮች ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡

በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ223 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ገቢ ተገኝቷል፡፡

ቢሮው ያለፈውን ግማሽ የበጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሰሞኑን በገመገመበት ወቅት የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ሰኢድ እንደገለጹት በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን ከአንድ ሚሊዮን 177 ሺህ የሚበልጡ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ጎብኝተዋል፡፡

ከጎብኚዎቹም መካከልም ከ67 ሺህ የሚበልጡት ከጀርመን፣ ከጣሊያን፣ ከኤዥያ፣ ከደቡብና ሰሜን አሜሪካ እንዲሁም ከአፍሪካ የተውጣጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ቀሪዎቹ ጎብኝዎች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ገልጸው ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከውጭ ሀገር በሁለት ሺህ ፣ በሀገር ውስጥ ደግሞ ከ371ሺህ በላይ ጎብኝዎች ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የላሊበላ፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የጭስ አባይ ፏፏቴና የጣና ገዳማትን ጨምሮ ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ከጎበኙ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ከ223 ሚሊዮን የሚበልጥ ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

የተገኘውም ገቢ ካለፈው ዓመት ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ጠቁመው ክልሉን የሚጎበኙ የቱሪስቶች ቆይታ ጊዜም በአማካኝ 10 ቀን ማድረስ እንደተቻለ አስታውቀዋል፡፡

ገቢውና የቱሪስት ፍሰቱ የጨመረው ቢሮው በከፈተው ድህረ ገጽ በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ማስተዋወቅ በመቻሉ እንደሆነ ኃላፊው አገልጸዋል፡፡

አዳዲስ የጉዞ መስመሮችን በማጥናትና በማስተዋወቅ የኮሙኒቲ ቱሪዝምን በማስፋፋት በተለይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ክልሉን ከጎበኙ ከ803 ሺህ የሚበልጡ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ከ166 ሚሊዮን የሚበልጥ ገቢ መገኘቱን ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡