53 ሺ በልመና ተሰማርተው የነበሩ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመለሱ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2004 (ዋኢማ) – ባለፉት ጥቂት ዓመታት 53 ሺ የሚሆኑ በልመና ተሰማርተው የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፤ ከተመላኞቹ መካከልም 16ሺዎቹ መደበኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው፡፡

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሸለመ እንዳስታወቁት ልመናን ከአገራችን ለማጥፋት መሥሪያ ቤቱ በልመና የተሠማሩ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ተመልሰው በልማት ሥራ እንዲሰማሩ እየተደረገ ነው፡፡

እንደ አቶ ግርማ ገለጻ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በቅርብ እየሠራ ይገኛል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤን ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤን ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ዳሬክተር አቶ የማነ ወ/ማሪያም በበኩላቸው ድርጅታቸው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር እየሠራ እንደሚገኝና በቅርቡም አንድ ሺ ስድስት መቶ በልመና የተሰማሩ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡