በሶማሌ ክልል የእናቶችንና የህፃናት ሞት መቀነሱ ተገለጸ

ጅጅጋ፤ የካቲት 21/2004 (ዋኢማ) ¬ – በሶማሌ ክልል ያለው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በክልሉ ይደርስ የነበረው የእናቶችንና የህፃናት ሞትን ለመቀነስ የጎላ ድርሻ እንደነበረው ተገለፀ፡፡ ፕሮግራሙን በሰፊው በሁሉም የአርብቶ አደሩ መንደር ለማዳረስ በክልሉ በየደረጃው የሚገኘው አመራርና የህብረተሰብ ክፍል ያልተቆጠበ ጥረት እንዲያደርጉም ተጠይቋል፡፡

በክልሉ ኘሮግራሙን የበለጠ ለማጠናከርና ሁሉንም የአርብቶ አደሮችን መንደር ተጠቃሚ ለማድረግ በተዘጋጀው የህዝብ ንቅናቄ መድረክ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዱፈታህ መሀሙድ እንደተናገሩት፤ በክልሉ እየተተገበረ ያለው የጤና ኤክስቴሽን ኘሮግራም የእናቶችንና የህፃናትን ሞት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ውጤት ተገኝቶበታል ፡፡

በክልሉ የኘሮግራሙን ተደራሽነት ይበልጥ በማስፋት አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ  አመራሮችና የተለያዩ ማህበራት  ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶ/ር የሱፍ መሀመድ በበኩላቸው፤ በክልሉ የጤና ኤክስቴንሽን ኘሮግራም ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ የእናቶችና ህፃናትን ህይወት መታደግ እየተቻለ ነው፡፡

ኘሮግራሙን  በ1 መቶ 35 የጤና  ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የተጀመረ መሆኑን ገልፀው፤ በአሁኑ ወቅት የባለሙያዎቹ ቁጥር  በአራት እጥፍ በማሳደግ በሁሉም ቀበሌዎች በማዳረስ  በክልሉ በ7 መቶ 13 ቀበሌዎች እየተተገበረ ነው፡፡