ሰብአዊ መብትን ለማስከበር የምክር ቤት አባላት ሚና የጎላ መሆኑ ተገለጸ ሰብአዊ መብትን ለማስከበር የምክር ቤት አባላት የጎላ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፤ የካቲት 22/2004 (ዋኢማ) – የዜጎች ሰብዓዊ መብትን  በማስከበር ኢትዮጵያ የነደፈቻቸውን የልማት እቅዶች ለማሳካት የምክርቤት አባላትት    ሚና የጎላ መሆኑ  ተገለፀ፡፡

 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለደቡብ ክልል ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት አባላት ያዘጋጀው የሁለት ቀናት ስልጠና ላይ  በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ኮሚሽነር ወይዘሮ አስማሩ በሪሁን እንደገለፁት የምክር ቤት አባላት ሰብዓዊ መብትን በማክበርና በማስከበር የአገሪቱን የልማት እቅዶች ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው።

 

ምክር ቤቶች ሕግ አውጪዎች እንደመሆናቸው በሚያወጧቸው ሕጎች፣ አዋጆችና ደንቦች እንዲሁም ከመረጧቸው ሕዝቦች ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት በሕገ መንግስቱ የተደነገጉ የሰብዓዊ መብቶች መከበራቸውንና በትክክል ተፈፃሚ መሆናቸውን መከታተልና መቆጣጠር እንዳለባቸውም ኮሚሽነሯ ጠቁመዋል።

 

እንደ ኮሚሽነሯ ማብራሪያ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱና ተጥሰው ሲገኙ ለማረም የምክር ቤት አባላት በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል።

 

በተለይ የህፃናት፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን  መብቶች ለማስከበር የጋራ ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል።

 

የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንድ ሶስተኛው ያህሉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ቢይዝም አሁንም ከድህነት፣ ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ከኋላቀር አመለካከቶች የተነሳ የመብት ጥሰቶች እንደሚታዩ ወይዘሮ አስማሩ ተናግረዋል።

 

እነዚህን ለማስቀረት ደግሞ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

 

የደቡብ፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ  ገነት ወልዴ በበኩላቸው ምክር ቤቱ በክልሉ ሕገ መንግስት በርካታ ኃላፊነቶች እንደተሰጡት አስታውሰው፤ የምክር ቤቱ አባላት እነዚህኑ ኃላፊነቶች በአግባቡ እንዲወጡ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

 

የምክር ቤቱ አባላት ስልጠናውን መነሻ በማድረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እንዲከላከሉም አሳስበዋል።

 

“ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር፣ በማስከበርና በማሟላት፣ ረገድ የክልል ምክር ቤት አባላት ሚና” በሚል በተዘጋጀው ስልጠና የሰብዓዊ መብት ፅንሰ ሀሳብና ታሪካዊ እድገት፣ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መብቶችና ሌሎች ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው የስልጠናው መርሀ ግብር ያሳያል።