በመላው አፍሪካ የቆዳ ንግድ ትርኢት ላይ ከ38 የተለያዩ የአለም አገራት የተውጣጡ 185 ድርጅቶች እየተሳተፉ ናቸው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2004 (ዋኢማ) – የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ባዘጋጀው 5ኛው የመላው አፍሪካ አለም አቀፍ የቆዳ ንግድ ትርኢት ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ38 የተለያዩ የአለም አገራት የተውጣጡ 185 ድርጅቶች እየተሳተፉ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ሚሌኒዬም አዳራሽ የተጀመረው የንግድ ትርኢት ለሦስት ቀናት ይቆያል፡፡

በንግድ ትርኢቱ ላይ ከቆዳ የተዘጋጁ የእጅ ጓንቶች፣ የኪስ ቦርሳ፣ የሴት ቦርሳዎች፣ ጫማዎች፣ የቆዳ ማልፊያ እና ማለስልሻ ማሽን አቅራቢ ኩባንያዎች፣ የቆዳና ሌጦ ኬሚካል አምራቾችና አስመጪዎች እንዲሁም ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ጋር በተያያዘ የቆዳና ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የመሳሰሉ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት እየተሳተፉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ቆዳዎች ኢንዱስትሪ ማህበር የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ጌቱ በትርኢቱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚካሄደው የመላው አፍሪካ የቆዳ የንግድ ትርኢት ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች በአንድ ጣራ ስር ሆነው የንግድ ስምምነቶችን ለማድረግ ያስችላል፡፡

እንዲሁም በቴክኖሎጂና በዘርፉ ያሉትን ወቅታዊ ጉዳዮች በተመለከተ መረጃ ለመለወዋጥ እና በጋራ ምክክር ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

በአሁኑ ወቅት እሴት የተጨመረባቸው ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ወደ ውጭ እየተላኩ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን በቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በአገሪቱ ከፍተኛ ለውጥ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አገሪቱ እሴት በመጨመር ወደ ውጭ የምትልካቸው የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው አውሮፓ፣
እስያ፣ አሜሪካ እና የተወሰኑ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን ምርቶች በስፋት እየተቀበሉ ናቸው።

የንግድ ትርኢቱ በኩባንያዎቹ መካከል አዳዲስ ገበያ ለማግኘት፣ የንግድ ስምምነቶችን ለመፈረራምና ወደፊት ለሚኖሩ የንግድ ግንኙነቶች የትውውቅ መድረክ ሆኖም ያገለግላል።

ትርኢቱ ላይ ከሚሳተፉ ድርጅቶች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው “የቤስት አፍሪካን ኤክስፖርት” ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሜሪ ሐደራ አንዷ ናቸው። ድርጅታቸው ወደ ቆዳ ኢንዱስትሪው ከተሰማራ ገና ጥቂት ወራት ቢሆነውም እስካሁን ድረስ የገበያ ችግር እንዳላጋጠመው ገልጸዋል።

በአገር ውስጥ ከቆዳ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና ማሽኖች ስራ ላይ በመዋላቸው በቆዳ ምርቶች ላይ የጥራቱ ሁኔታ መሻሻል እያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል።

ድርጅታቸው በእጅ የተሰሩ በቀን እስከ 60 ጥንድ ጫማዎችን እያመረተ ለገበያ እንደሚያቀርብ የገለጹት ወይዘሮ ሜሪ ጫማዎቹ በተነጻጻሪ ዋጋቸው ጭማሪ እያሳዩ ቢሆንም ከውጭ ከሚገቡት የጫማ ምርቶች አንጻር ሲታይ ለአገር ውስጥ ተጠቃሚው ዋጋው በጣም መልካም የሚባል መሆኑን ገልጸዋል።

ጥሬን ቆዳ ወደ ውጭ መላክ በመቆሙ በቆዳው ዘርፍ ለተሰማሩ የአገር ውስጥ አምራቾች ምርቱን እንደ ልብ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘትም ረድቷቸዋል።

የኮልባ የቆዳና ማልፊያና ማለስለሻ ኩባንያ የምርትና ቴክኒክ ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረሚካኤል መገርሳ በበኩላቸው ወደ ፋብሪካው ከሚመጡ ጥሬ ቆዳዎች መካከል አብዛኞቹ ከፍተኛ የጥራት ችግር በስፋት የሚስተዋልባቸው እንደሆኑ ተናግረዋል።

ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ያሉት ደግሞ በተለይ በበግ ቆዳዎች ላይ እከክን በመሰሉ ጥገኛ ህዋሳት የሚጠቁ በመሆናቸው ጥሬ ቆዳው ፋብሪካ ገብቶ በሚሰራበት ወቅት የሚፈለገው ጥራት አይገኝም። ይህም በዘርፉ የሚጠበቀውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል።

አቶ ገብረሚካኤል እንደሚሉት ይህን ቀስ በቀስ ለማስወገድና የሚፈለገውን ጥራት ለማግኘት የግብርና ሚኒስቴር እና የሚመለከታቸው አካላት በእንስሳት አያያዝ እና አጠባበቅ ዙሪያ ለአርብቶ አደሮች ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

ትርኢቱ ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙ የውጭ ኩንያዎች መካከል አንዱ ኢታልከም የተባለው የኢጣሊያ የቆዳ ኬሚሎች አቅራቢ አንዱ ነው። የኩባንያው ተወካይ ማሪኖ ኩንስሎ እንደሚሉት ኩባንያው በኢትዮጵያ በሚዘጋጀው የቆዳ ንግድ ትርኢት ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ኩባንያቸው ላለቀላቸው የቆዳ ምርቶች የሚሆኑ ኬሚካሎችን የሚያመረት ሲሆን በኢትዮጵያ በቆዳው ኢንዱስትሪ መነቃቃት በመኖሩ በአገር ውስጥ ኬሚካሎችን የሚያከፋፍል ድርጅት በማፈላለግ ላይ ነው።

በትርኢቱ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ መንግስት ለቆዳው ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱንና አገሪቱ በመስኩ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ባለሃብቶችን እንደምትፈልግ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።