የግብርናው መርሀ- ግብር የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ስቧል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2004 (ዋኢማ) – ባለፈው ጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም ሰባት ቢሊዮን የደረሰው የዓለም ሕዝብ ብዙም ሳይቆይ ዘጠኝ ቢሊዮን እንደሚደርስ እየተነገረ ነው። ዕድገቱ በየዓመቱ ከ80 ሚሊዮን በላይ በሆነ ቁጥር እየጨመረ እንደሆነም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

ከዓለም ሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የሚያድገውን የምግብ ፍላጎት ለማሟላት እ.አ.አ ከ2050 በፊት የምግብ ምርታማነት በሰባ በመቶ ማደግ እንዳለበትም ነው የሚመከረው።
በዓለም ላይ ያለው ረሃብ እ.አ.አ. ከ1990ዎቹ አጋማሽ በፊት በነበሩት አስርት ዓመታት የመቀነስ ሁኔታ ያሳየ ቢሆንም ከዛ በኋላ ግን የመጨመር ሁኔታ ታይቶበታል። በተለይ እ.አ.አ በ2008 የምግብ ዋጋ ሲንር ጉዳዩ የከፋ ሁኔታ ላይ ደርሶ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። እንደውም እ.አ.አ በ2011 ለረሃብ የተጋለጡት ሰዎች ቁጥር 925 ሚሊዮን ደርሶ ነበር። በወቅቱ ለረሃብ ከተጋለጡትም ውስጥ 98 በመቶ የሚሆኑት በታዳጊ አገራት እንደሚገኙ ነበር የተነገረው። ከእነዚህ ውስጥም ሁለት ሦስተኛው በባንግላዴሽ፣ ቻይና፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ኢትዮጵያ፣ ህንድ፣ ኢንዶኔዥያና ፓኪስታን ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት በአየር ንብረት ለውጥም ሆነ በሌላ ምርታማነት ላይ የሚደርስ ተጽዕኖ የመጀመሪያ ተጠቂዎች ድሆችና ለችግሩ ተጋላጭ አካባቢዎች መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ያደረገው የዓለም የኢኮኖሚ ማኅበራዊ ጥናት ያመለክታል።
አገራቱ በየራሳቸው መንገድ ችግሩን ለመቅረፍ የሚረዳ አቅጣጫ ቀይሰው እየተንቀሳቀሱ ነው።

በኢትዮጵያም የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችና ውጤቶቻቸው ይፋ እየሆኑ መጥተዋል። ለዚህ ደግሞ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ርብርብ እንዳለበትም ነው የሚነገረው።

በዚህ እንቅስቃሴም 85 በመቶ ለሆነው የአገሪቱ ሕዝብ መተዳደሪያ የሆነውን የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደተቻለ ይነገራል። ለአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት 41 በመቶ ድርሻ የሚያበረክተው ለወጪ ንግድ ደግሞ 90 በመቶ የሚሆነውን ግብርና ትኩረት እንደሚሻም ነው ብዙዎች የሚስማሙት።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያለው የግብርና ምርት 95 በመቶ የሚሆነው ከትናንሽ እርሻዎች የሚገኝ ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆነችበት የእንስሳት ሀብቷም 25 በመቶ በተደጋጋሚ ድርቅ በሚያጠቃቸው በደረቃማ አካባቢዎች ይገኛል።
ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በአበረታች ሁኔታ እያደገ ያለው ግብርና በዓመት በአማካኝ በ10 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ በአጠቃላይ የአፍሪካ ግብርና ልማት ፕሮግራም ዕቅድ የበለጠ አፈጻጸም ታይቶበታል ለግብርናው ዘርፍ እየፈሰሰ ያለው ኢንቨስትመንት የብሔራዊ በጀቱ 15 በመቶ ሲሆን፤ በአጠቃላይ የአፍሪካ ግብርና ልማት ፕሮግራም (CAADP) ከታቀደው 10 በመቶ የበለጠ ነውም ተብሏል። ይህን አገሪቱ በዓለም ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለማለፍ እያደረገች ያለችውን ጥረት ያመለክታል። የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የምግብ ዋስትና ላልተረጋገጠባቸው አካባቢዎች የተሻለ ውጤት ለማምጣት ተስፋ እንደተጣለበት ነው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መረጃ የሚያመለክተው።

ተለጥጦ የተቀመጠውና የተሻለ የተባለለት የአገሪቱ የግብርና ፕሮግራምና የኢንቨስትመንት ፍሬም እንዲሁ ረሃብን በመቀነስ በኩል እያስገኘ ያለው ውጤት ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት የሳበና የዓለም የምግብ ቀውስ ፈንድን በሰፊው እንዲያገኝ ዕድል የሰጠ መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ደግሞ አገሪቱ በግብርናና ምግብ ሥርዓት ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማለፍ ያስችላታል ነው የተባለው።
የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ካልቀጠለና በፍጥነት ውጤታማ መሆን ካልቻለች ግን የምግብ ዋጋ ንረት አገሪቷን ሊጎዳት ይችላል። ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸው ዋና ዋና ምግቦች እ.አ.አ በ2030 ከ120 እስከ 180 በመቶ የዋጋ ንረት ሊከሰትባቸው ይችላል። በዚህ ወቅት ደግሞ የአየር ንብረት ለውጡ በአገር ውስጥ ምርቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው ስለሚችል ችግሩን እንደሚያባብሰው ነው የሚነገረው።
በከፍተኛ ቦታዎች ያለው የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር እየጨመረና የሕዝብ ጥግግቱ እያደገ የሚሄድ በመሆኑም ለእርሻ የሚውሉ መሬቶች እያነሱ ይሄዳሉ። ከስድስት እስከ ስምንት የቤተሰብ አባል የሚያስተዳድሩት 40 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛ አርሶ አደሮች ከግማሽ ሄክታር በላይ የማያርሱ ናቸው። በደረቃማ አካባቢ ደግሞ የግጦሽ መሬት ሽሚያ ሊኖር ስለሚችል መሬት እንዲራቆትና ለድርቅ እንዲጋለጥ ሊያደርግ እንደሚችልም ተገምቷል።

ለሴቶችና አነስተኛ መሬት ላላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ካልተሰጠ ረሃብን ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የታለመውን ግብ ማሳካት ይከብዳል። ጥናቶች እንደሚጠቁሙትም ሴቶች መሬት የማግኘት ሁኔታ ዝቅተኛ መሆን፣ በገጠር የጉልበት ሠራተኞች በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ የገንዘብ አቅርቦት ማነስ፣ የማኅበራዊ ሀብትና ቴክኖሎጂ እጥረት በግብርናው ውጤታማነት ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ ያሉ ጉዳዮች ናቸው።

በአገሪቱ ዋና ዋና የምግብ ሰብሎች ለማምረት የታረሰው መሬት በ1997 ዓ.ም ከነበረበት ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር በ2002 ዓ.ም ወደ 11 ነጥብ 25 ሚሊዮን ሄክታር አድጓል። ከነዚህ ሰብሎች የተገኘው የምርት መጠንም ከ119 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ወደ 191 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ብሏል። ምርታማነቱም ቢሆን በሄክታር ከ12 ነጥብ አንድ ኩንታል ወደ 17 ኩንታል ከፍ ማለቱን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መነሻ ሰነድ ያመለክታል።
ዘርፉ በመንግሥት በተሰጠው ትኩረት ለአርሶ አደሮች በኤክስቴንሽን የሚሰሩ ሥራዎችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፍ ሲሰጥ ነበር። የትምህርትና ሥልጠና ሥራዎችም ቢሆኑ የዘርፉን ምርታማነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማሳደግ በሚያስችል መልኩ እንዲሆኑ መደረጉንም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሂደቱም ቢሆን በመንደር የማሰባሰብ ፕሮግራምና በልማት ሴፍቲኔት እየታገዘ ብዙዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ዕድገት በማረጋገጥ ድህነትን ለማስወገድና የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ለማሳካት ተስፋ የተጣለበት ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትልቅ ትኩረት አግኝቷል። በእቅዱ እንደተቀመጠውም የአርሶ አደሩ እርሻ ዋነኛው የግብርና ዕድገት ምንጭና መሠረት ሆኖ ይቀጥላል። በግብርናና ገጠር ልማት የፖሊሲ አቅጣጫ የሰው ጉልበትንና መሬትን በአግባቡ መጠቀም ቁልፍ ጉዳይ ሆኗል። አርሶ አደሩ አነስተኛ ካፒታል የሚጠይቁ ዘመናዊ የግብርና ልማት ቴክኖሎጂዎችን በብቃት እንዲጠቀም ማስቻልና አዳዲስ የግብርና አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረግም ሌሎች ተጠቃሽና ትኩረት ያገኙ ጉዳዮች እንደሆኑም ነው ሰነዱ የሚጠቅሰው።
የግሉ ዘርፍ በግብርና ልማት የሚኖረው ድርሻም ከፍተኛ እመርታን በማስመዝገብ አንድ መሠረታዊ የግብርና ዕድገት ምንጭ እንዲሆን ማድረግም ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው።

አርሶ አደሩ ይከተለው የነበረውን ከእጅ ወደ አፍ የሆነየግብርና ዘዴ ወደ ገበያ መር ግብርና እንዲቀይር የተደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሰነዱ ያትታል። ለዚህ ደግሞ ምርጥ አርሶ አደሮች የሚጠቀሙበትን ቴክኖሎጂ ማስፋፋት፣ የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅና የመስኖ ልማትን ማጠናከርና የተሻለ ዋጋ ወዳላቸው ምርቶች ማሸጋገር እንደ አቅጣጫ ተይዘዋል።
በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚከናወኑ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ተግባራት የጋራ መሠረተ ልማት ግንባታውንና ይህንኑ ማሳካት በሚያስችል መልኩ እንዲከናወን ጥረት እንደሚደረግም ነው የተመለከተው።

ለመስኖ ሥራ አመቺ በሆኑ አካባቢዎች የመስኖ ልማትን በመተግበር አርብቶ አደሮችን በፈቃዳቸው ማስፈርም ሌላው ተግባር እንዲሆን ታስቧል። የተሻሻሉ የአካባቢ የእንስሳት ዝርያዎችን በመምረጥና በማሠራጨት፣ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ከአርብቶ አደሩ የአኗኗር ዘይቤ ጋር ባገናዘበና ተንቀሳቃሽ አገልግሎትንም ባካተተ መልኩ እንዲስፋፋ፣ ሙያተኞችም በአቅምና በቁጥር እንዲጠናከሩ ለማድረግ የተጠናከረ ሥራ ይሰራል ሲል አዘ ዘግቧል።