ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የጋራ ስትራተጂክ ፓርትነርሺፕ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2004 (ዋኢማ) – የመጀመሪያው የኢትዮ ደቡብ ሱዳን የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በደቡብ ሱዳን ርዕሰ ከተማ ጁባ ለአምስት ቀናት ተካሂዷል፡፡

በሁለት ደረጃ ተከፋፍሎ የተካሄደው የሁለቱ ሀገራት የጋራ ከሚሽን ስብሰባ የመጀመሪያው በሁለቱ ሀገራት ኤክስፐርቶች መካከል የተካሄደ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሚኒስትሮች ደረጃ የተደረገ ነው፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር አቶ በረከት ስምዖንን ጨምሮ ሌሎች ሚኒስትሮችና የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችን ያካተተ ነው፡፡

በደቡብ ሱዳን በኩል የደቡብ ሱዳን ሪፖብሊክ የውጭ ጉዳይ እና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትርን ጨምሮ ሌሎች የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተካፍለውበታል፡፡

በውይይቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንዳሉት የሁለቱ የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ለሚያከናውኗቸው ስራዎች ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን ህዝብና መንግስት ሀገሪቱን ለመገንባት ለሚያደርጉት ልማታዊ እንቅስቃሴም ኢትዮጵያ ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን ከሰሜን ሱዳን በጋራ ያላትን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረትም እንደምትደግፍ አቶ ኃይለማሪያም ጠቁመዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን ሪፖብሊክ የውጭ ጉዳይና የአለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሚስተር ናሂይል ዴንግ ናሂይል በበኩላችው ኢትዮጵያ በሰሜንና ደቡብ ሱዳን መካከል ያሉትን አንዳንድ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የምታደርግው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ኢሬቴድ ዘገባ በመጀመሪያው የኢትዮ ደቡብ ሱዳን የጋራ ሚኒስትሮች ስብሰባ ሁለቱ ሀገራት የጋራ ስትራቴጂክ ፓርትነርሽፕ ስምምነትም ፈርመዋል፡፡