ጋዜጠኛ ተስፋዬ ማሞ ወ/ሚካኤል ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

አዲስ አበባ፤የካቲት 29 2004/ዋኢማ/ – በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በዶክመንተሪ ፊልም አዘጋጅነት ሲያገለግል የነበረው ጋዜጠኛ ተስፋዬ ማሞ ወ/ሚካኤል ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡

ከአባቱ ከአቶ ማሞ ወልደ ሚካኤል ከእናቱ ከወይዘሮ ጥሩነሽ ተሾመ መጋቢት 15 ቀን 1959 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለደው ጋዜጠኛ ተስፋዬ ማሞ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ከተማ ተከታትሏል፡፡

ጋዜጠኛ ተስፋዬ ማሞ ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ በቋንቋና ሥነ ጽሁፍ በዲፕሎማ፣ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት አድቫስድ ዲፕሎማ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ  በቋንቋና ሥነ ጽሁፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል፡፡

በሥራ ዓለምም በጉችሬ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት፣ በአብይ ዓዲ መምህራን ኮሌጅ በሌክቸረርነት፣ በሩህ ጋዜጣና መጽሔት በዋና አዘጋጀነት፣ በትራንስፖርት ባለሥልጣን በሥነ ጽሁፍ ኤክስፐርትነት አገልግሏል፡፡

ላለፉት ስድስት ዓመታት በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በዶክመንተሪ ፊልም አዘጋጅነት ያገለገለው ጋዜጠኛ ተስፋዬ ማሞ በኢትዮዽያ ቴሌቪዥን ሲተላለፍ  በነበረው ሀገሬ ፕሮግራም  ከሃምሳ በላይ ዘጋቢ ፊልሞችን አዘጋጅቶ ለእይታ እንዲቀርቡ አድርጓል፡፡

ጋዜጠኛ ተስፋዬ ማሞ በአዘጋጃቸው ዘጋቢ ፊልሞች  የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህልና ታሪክ እንዲታወቅ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ የሆነ ሙያዊ አስተዋጾ አበርክቷል፡፡

ጋዜጠኛ ተስፋዬ ማሞ ባደረበት ህመም በጦር ኃይሎችና በኮሪያ ሆስፒታሎች በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በተወለደ በ45 ዓመቱ የካቲት 27 2004 ዓ.ም አርፏል፡፡

የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በአዲስ አበባ ላፍቶ ሚካኤል ወዳጅ ዘመዶቹና የሙያ ባልደረቦቹ በተገኙበት የካቲት 28 2004 ዓ.ም  ተፈጽሟል፡፡

ጋዜጠኛ ተስፋዬ  ማሞ ባለትዳርና የአንድ ሴትና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበረ፡፡

በጋዜጠኛ ተስፋዬ ማሞ ሞት የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ማነጅመንትና ሠራተኞች የተሰማቸውን ጥልቅ አዘን እየገለጹ ለቤተሰቡና ለወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናትን ይመኛሉ፡፡