በግማሽ የበጀት ዓመቱ 137ሺ ቶን ስኳር ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2004/ዋኢማ/- የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኤጀንሲ በግማሽ የበጀት ዓመቱ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላው ወጪ በማድረግ 137ሺ ቶን ስኳር ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለህብረተሰቡ ማከፋፈሉን አስታወቀ።

የኤጀንሲው የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ይልማ ጥበቡ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በሀገር ውስጥ ያለው የስኳር ፍላጎትና አቅርቦት ሊመጣጠን ባለመቻሉ ኤጀንሲው ከውጭ በማስገባት ለማመጣጠን ጥረት አድርጓል።

ቀደም ብለው የተቋቋሙት የመተሃራ፣ ወንጂ ሸዋና የፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች በአመት ሶስት መቶ ሺ ቶን ስኳር ቢያመርቱም በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የስኳር ፍላጎት አምስት መቶ ሺ ቶን በመሆኑ ፍላጎትና አቅርቦት ሊመጣጠን አይችልም።

“መንግስት ስኳርን ከውጪ እንዲያስገባ ያደረገው በሀገር ውስጥ ያለው የስኳር ፍላጎትን ለማሟላት ሲል ነው” በማለት አቶ ይልማ ይገልፃሉ። 

እንደ አቶ ይልማ ገለፃ ከውጪ የገባውን ስኳር በመላው ሀገሪቱ በተመጣጣኝ ዋጋ መከፋፈሉን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት በቂ የስኳር ክምችት በመጋዘን በመኖሩ የስኳር እጥረት ሊከሰት እንደማይችል ተናግረዋል።

መንግስት በሚቀጥሉት ሶስትና አራት አመታት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን በላይ ስኳር በማምረት ከሀገር ውስጥ አቅርቦት በተጨማሪ ለውጪው ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ይልማ ገለፃ ሀገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ስኳርን ለውጭ ገቢያ ከሚያቀረቡ 10 ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ እቅድ እንዳላት ገልፀዋል።

እቅዱን ለማሳካትም በትግራይ፣ አፋር፣ አማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ዘጠኝ የሚሆኑ የስኳር ፋብሪካዎችን በማቋቋም ላይ እንደምትገኝ ዳይሬክተሩ መግለፃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።