የፌዴራል ሥርዓቱ የዜጎችን የአንድነት መንፈስ አጠናክሯል- አፈ ጉባዔው

በኢትዮጵያ የተዘረጋው የፌዴራል ሥርዓት የዜጎችን የአንድነት መንፈስ በማጠናከር ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለፀ፡፡

የፌዴራሊዝም ሥርዓት ዜጎች ማንነታቸው ተከብሮና ተረጋግጦ የቋንቋና የእምነት ልዩነት ሳይገድባቸው ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ማስቻሉን የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተ ለዋልታ ገልፀዋል፡፡

ዜጎች ፈቅደውና ወደውት ዕውን የሆነ ሥርዓት መሆኑን አፈ ጉባዔው ጠቁመው የልማቱ ፍትሃዊ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ነው ያስረዱት፡፡ ባለፉት ዓመታትም ይሔው እውነታ በተግባር መረጋገጡን አስታውሰዋል፡፡

ህዝቡ በህገ መንግስቱ የተረጋገጡለትን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ዕውን በማድረግ በኩልም የፌዴራል ሥርዓቱ የላቀ ሚና መጫወቱን አቶ ያለው ተናግረዋል፡፡

አቶ ያለው እንዳሉት የአገሪቱ ብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመቻቻልና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረት አካሄድን እንዲከተሉም አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን ተከትሎ ሁሉም ክልሎች በከፍተኛ የልማት ጎዳና ላይ መረማማድ ችለዋል፡፡ ትክክለኛና ተመራጭ የዕድገት መስመር እንደሆነም በተመዘገቡት ውጤቶች ተረጋግጧል፡፡

ሥርዓቱ ቀደም ሲል ቁልቂሊት ሲጓዝ የነበረውን የአገሪቷን የዕድገት አቅጣጫ በመለወጥ ከፍተኛ ዕድገትና ልማት እንዲመዘገብ አስችሏል፡፡ ሁሉም የአገሪቲ ክልሎች  በመሰረተ ልማት እንዲተሳሰሩና ልማታቸውን እንዲያፋጥኑም ማገዙን አፈ ጉባዔው አስረድተዋል፡፡

በፌዴራል ሥርዓቱ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም አፈ ጉባዔው አስገንዝበዋል፡፡ ያልተማከለ አስተዳደርን በመዘርጋት ግልፅነትና ተጠያቂነትን የተላበሰ አሰራርና አስተዳደርን በመዘርጋት ከፍተኛ ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ አድርጓል፡፡

የፌዴራል ሥርዓት አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም አገራት ተግባራዊ መደረጉን አቶ ያለው አውስተው ኢትዮጵያም ከአገሪቱ ነባራዊ እውነታ ጋር በሚጣጣም መልኩ ህግ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት በህዝቡ ፈቃደኝነት ሥርዓቱ መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡