በአገሪቱ አንድንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከት በተመለከተ ለዋኢማ አስተያየታቸውን የሠጡት አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ህብረተሰቡ ለመንግሥት የሚያቀርበው ጥያቄም ካለ በሰላማዊ መንገድና ህገመንግሥቱን በተከተለ መልኩ በማድረግ ጥያቄ የሚያነሱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከመንግሥት ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ብለዋል ።
በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን በማስጠበቅ በአገሪቱ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ እውን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎቹ አክለው ገልጸዋል ።
እንደ ነዋሪዎቹ አስተያየት መንግሥትና ህዝብ በጋራ በመሆን በአገሪቱ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በግልጽ ውይይት በማድረግ የታዩ ክፍተቶችንም ጠቃሚ በሆነ መልኩ ለመድፈን መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነው አለባቸው ተስፋው እንዳለው በአገሪቱ በከፍተኛ ውጭ ምንዛሪ የተገነቡ የመሠረተ ልማቶች በሁከት ምክንያት መውደም እንደሌለባቸውና ከዚህም ተግባር ማንም እንደማይጠቀም ስለዚህም ሁሉም ዜጋ ለአገር ልማትና ዕድገት ሲል ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው አመልክቷል ።
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ሙሉ ተክላይ በበኩላቸው የአገሪቱን ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ማረጋጋጥ የመንግሥት ብቻ የሚተው ተግባር ባለመሆኑ ሁሉም ዜጋ የበኩሉም ሚና መጫወት እንዳለበት ጠቁማ መንግሥት ሁልጊዜ ችግሮች እየተባባሱ ከመምጣታቸው በፊት አስቀድሞ ሊቆጣጣራቸው ይገባል ብላላች ።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ የሆነቺው አበባ ሰለሞን በበኩሏ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱት ሁከቶች ህብረተሰቡ በመንግሥት የአስተዳደር አካላት የሚያገኘው አገልግሎት ስላላረካው በመሆኑ መንግሥት ከላይ እስከ ታች ባሉት የአስተዳደር መዋቅሮች መልካም አስተዳደርን ማስፈን እንደሚገባው ገልጻለች ።
ሁሉም አስተያያት ሠጪዎች እንደሚሉት ህብረተሰቡ በመንግሥት እውቅና ባልተሰጣቸውና ኃላፊነት ባልተወሰደባቸው የሰላማዊ ሰልፎችና ተቃውሞዎች መሳተፍ እንደሌለበት ገልጸው መንግሥት በበኩሉ ግን ለዜጎች በተለይም ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል ።