11ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ቅድመ ዝግጅት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመለከተ፡፡
የበዓሉ አስተናጋጅ የሆነችው ሐረር ከተማ በዓሉን በድምቀት ለማክበር የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑን ፌዴሬሽን ምክር ቤት ገልጿል፡፡
የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ለበዓሉ ዝግጅት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት አዳራሾችና የእንግዶች ማረፊያ የመሳሳሉ ቤቶችን የማዘጋጀት ሥራ እያከናወነ እንደሆነ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተ ለዋልታ ገልፀዋል፡፡
በተለይም ከተማዋ ብዙ ሰው ማስተናገድ የሚችል አዳራሽ እንዳልነበራት አስታውሰው አሁን በዓሉን ምክንያት በማድረግ ትልቅ አዳራሽ እየተገነባ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች ውስን መሆናቸውን አፈ ጉባዔው ጠቁመው አሁን ላይ በርካታ ሆቴሎች መገንባታቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የበዓሉ ሥነ ሥርዓት የሚከበርበት ስታዲየምም እየተዘጋጀ ነው፡፡
የከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ፤ የፅዳትና የውበት ሥራዎችም በስፋት መከናወናቸውን አቶ ያለው ተናግረዋል፡፡ በዚህ በኩል ህብረተሰቡም በስፋት መሳተፉ ነው የተመለከተው፡፡
ክልሉ በዓሉን በተለያዩ የልማት ሥራዎች ለማክበር የጀመራቸው ሥራዎችም በተያዘላቸው ዕቅድ መሰረት እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል- አፈ ጉባዔው፡፡
በ2010 ዓ.ም ግንባታውን ለማጠናቀቅ እየተገነባ የሚገኘው ትልቅ ሪፈራል ሆስፒታል ቀደም ብሎ በማጠናቀቅ ከተቻለም በበዓሉ ቀን ለማስመረቅ ግንባታው እየተፋጠነ ይገኛል፡፡
የወጣት ማዕከላትና የፖሊስ ጣቢያዎችን የመሳሰሉ የተለያዩ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ግንባታም ተከናውኗል፡፡
በክልሉ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተገነቡትና የተከናወኑት የልማት ሥራዎች ከ10 ዓመት በኋላ ሊከናወኑ የሚችሉ እንደነበር አቶ ያለው ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም በዓሉ ልማትን ለማፋጠንም ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት አስረድተዋል፡፡
ቀደም ሲል በዓሉን ያስተናገዱ ክልሎችም ከፍተኛ የልማት ሥራዎችን በስፋት ማከናወናቸውን አስታውሰዋል፡፡የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔን ጨምሮ የተለያዩ አካላት የክልሉን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በቅርቡ መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡