የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውሳኔ አግባብ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስልጣንን በአግባቡ ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም አለማዋል የስርዓቱ አደጋ እንደሆነ ማየቱ ለቀጣይ እርምጃው ወሳኝ መሆኑን  የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የመንግስት ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርአቱ ቁልፍ ችግር መሆኑን እንደለየ ሁሉ ለመፍትሄው አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል።

በተለይ ላለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የተረጋገጠውን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል ድርጅቱ ችግሩን በፍጥነት ፈትቶ ወደ ሥራ መግባት እንዳለበት አመልክተዋል።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያለፉትን 15 ዓመታት የለውጥ ጉዞ ገምግሞ ያሳለፈውን ድርጅታዊ ውሳኔ አስመልክተው አስተያየታቸውን ከሰጡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች መካከል መምህር ምንዳ ተክሉ አንዱ ናቸው፡፡

እሳቸው እንደተናገሩት፣ ባለፉት 25 ዓመታት በመላው ሀገሪቱ ትርጉም ያላቸው ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ  እድገቶች ተመዝግበዋል።

ይሁንና አንዳንዴ ነዋሪው ለሚያነሳቸው የመልክም አስተዳደር ችግር ጥያቄዎች በአፋጣኝ ተገቢ ምላሽ አለመስጠት በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታ እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የዜጎችን ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ወጥተው ሥራ ላይ ቢውሉም በአንዳንድ አመራሮች ዘንድ እየተስተዋለ ያለው ሥልጣንን ለግል ጥቅም  የማዋል አባዜ በነዋሪው ዘንድ ቅሬታ ሲፈጥር መቆየቱን መምህር ምንዳ አስታውሰዋል።

"የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ይህን በተጨባጭ ገምግሞ ለሥርአቱ እንቅፋት መሆኑን ድምዳሜ ላይ መድረሱ ተገቢና አግባብ ያለው ከመሆኑ በተጨማሪ ለመፍትሄው ይረዳል" ብለዋል።

ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ በጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ ዘርፍ በመደራጀት በሥራ ላይ የተሰማራው ወጣት ሳሊም አብዱላኪም፣ የተማረ ወጣት በሀገሪቱ ልማቶች ላይ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ይበልጥ መጠናከር እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡

"ኢህአዴግ ለሀገር ሰላምና ዕድገት የሚጠቅሙ ፖሊሲዎች አውጥቷል፤ ከሕዝብ የሚነሱ ችግሮችንም ይቀበላል። ነገር ግን ችግሮቹ በአግባቡ መፈታታቸውን ታች ድረስ ወርዶ በመከታተል በኩል ሰፊ ክፍተት አለበት" የሚል ሃሳብም ሰንዝሯል።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ራሱን ያየበት መንገድ ተስፋ እንደሚሰጥ የገለጸው ወጣቱ፣ በቀጣይ ከሕዝብና ከሀገር ጥቅም በበለጠ ለግል ጥቅማቸው ቅድሚያ በመስጠት ሕብረተሰቡን  በሚያማርሩ የሥራ ኃላፊዎች ላይ አሰተማሪ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

አቶ ገዛኽኝ ወንድሙ የተባሉ የሥነልቦና ባለሙያው በበኩላቸው፣ የኢህአዴግ መንግስት በመላው ሀገሪቱ በሁሉም የልማት መስክ አንጸባራቂ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

ለልማት የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ውጤት መገኘቱን ጠቁመው፣ ልማቱን ይበልጥ አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ በአሁኑ ወቅት ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርአቱን የሚፈታተኑ አካላትን ማስወገድ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢህአዴግ ችግሩን ለመፍታት ውስጡን ከመፈተሽ መጀመሩ ተገቢ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ገዛኽኝ፣ በቀጣይ በኪራይ ሰብሳቢዎችና በሙስና ውስጥ በተዘፈቁ ባለስልጣናት ላይ ድርጅቱ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በማጠናከር ተአማኒነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት አስረድተዋል።

እንደ አቶ ገዛኽኝ ገለጻ፣ ድርጅቱ በቀጣይም ውጤታማ እየሆነ እንዲመጣ፣ የጀመረውን የለውጥ አቅጣጫ የሚያደናቅፉትን እያጠራ መምጣት አለበት።የመንግስት ስልጣንን ለሕዝብ ጥቅም የሚያውሉ አመራሮችን በየደረጃው ማጠናከር እንዳለበትም አመልክተዋል።

አቶ መሐመድ ሐሰን የተባሉ አዛውንት በበኩላቸው "በአንዳንድ የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች ስልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል በስፋት የሚታይ በመሆኑ ችግሩን በተቀናጀ አግባብ መፍታት ለነገ የሚተው አይደለም" ብለዋል፡፡

"በድሬዳዋ አስተዳደር የሕዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች ይፈታሉ ተብለው በብዙ ሚሊዮን ብር በመተግበር ላይ የሚገኙ የጤና፣ የመንገድና የድልድይ ፕሮጀክቶች የግል ጥቅማቸውን በሚያስቀድሙ የሥራ ኃላፊዎች መጓተታቸው የዚህ ማሳያ ናቸው" ብለዋል፡፡

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የመንግስት ስልጣንን ለግል ኑሮ ማሻሻያ ለማድረግ የሚታየው ዝንባሌ ስህተት መሆኑን አምኖ ለማረም ተጨማሪ እርምጃም ለመውሰድ ውሳኔ ላይ መድረሱን አድንቀዋል።

ውሳኔው ተግባራዊ ሆኖ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣም በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት ከሕብረተሰቡ ጋር ተባብረውና ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት። 

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አብዱጀባር አብዱልሰመድ የሕዝቡን ጥያቄዎች በፍጥነት ለመመለስና የተጀመሩትን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለማስቀጠል መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአስተዳደሩ ከኪራይ ሰብሳቢነትና ከብልሹ አሠራሮች ጋር የተያያዙ ችግሮችን የመፍታት ሥራ መጀመሩን ጠቁመው፣ ይህም ትርጉም ያለው ለውጥ  እንዲያመጣ ሕዝቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡(ኢዜአ)