ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ አስታወቁ

ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት የተካሄደው ተሃድሶ በልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ረገድ ቀላል የማይባል ውጤት በማስመዝገብ አገሪቱን ያስፈነጠረ ቢሆንም በዚሁ ሂደት የተለያዩ ተግዳራቶች በመከሰታቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) ምክር ቤት ጥልቅ ተሃድሶ እንዲደረግ መወሰኑን  ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ አስታወቁ። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በዛሬው እለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት  አገሪቱ  ባለፉት አስራ አምስት  የተሃድሶ ዓመታት ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገ ፈጣን እድገት ማስመዝገብ ችላለች። 

ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት ከድህነት ወለል በታች ይኖር የነበረው የአገራችን ህዝ በግማሽ መቀነሱ የዚህ  እድገት ውጤት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። 

እድገቱ  በህዝብ ዘንደ የፈጠረው ከፍተኛ የተጠቃሚነት ፍላጎትም በአንዳንድ የአማራና የኦረሚያ አካባቢዎች ለተፈጠሩ   ሁከት  አንዱ መንስኤ መሆኑን ጠቁመው በዋናነት ግን  በአመራር  ውስጥ የተፈጠረው የግል ጥቅም ፍላጎት  ማደግ  መሆኑን ገልጸዋል። 

ህዝብ ስልጣኑን ሲሰጠን በቅንነት እንድናገለግለውና በአገሪቱ  መሰረታዊ ለውጥ እንድናመጣ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም  በመንግስትም ሆነ በድርጅት  ስልጣንን ያለአግባብ የማዋል ተግዳሮት መገምገሙንአስታውሰው  ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ማድረግ አለበት ብለዋል። 

የተጠቀሱት ችግሮች እንዳሉ ሆነው ለዘመናት የአገሪቱን ውድቀት የሚሹ የኢትዮጵያ ጠላቶች አገሪቱን ለማተራመስና ልማቷን ለማደናቀፍ እያደረጉ ያለው  ጥረትም  ለችግሩ መባባስ ምክንያት እንደሆነ ጠቁመው ህብረተሰቡ ሰላሙን እንዲጠብቅ ጥሪ አስተላልፈዋል።