አራተኛው አገር አቀፍ የወጣቶች የተሳትፎና ንቅናቄ ጉባዔ ‹‹የወጣቶች የተደራጀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለህዳሴያችን›› በሚል መርህ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡
በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ጉባዔ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከወጣቶች ጋር መግባባትን መፍጠርን ዓላማው ማድረጉ ተመለክቷል፡፡
ጉባዔው ወጣቶች በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ ያሉባቸውን ችግሮች በማንሳትና በመወያየት ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያግዛልም ተብሏል፡፡
የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ወጣቶች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት ከፍተኛ አካላት ጋር በግንባር በመገናኘት ችግሮቻቸውን በመጠቆም የመፍትሔ አካል በመሆን የሚሳተፉበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡
የተጀመረውን ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ዕደገት በማስቀጠል የስርዓቱ አደጋ የሆኑትን ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር እጥረት ችግሮችን በወጣቱ ተሳትፎ የመፍታት ዓላማንም ያዘለ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዛሬው የወጣቶች ውይይትም የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት ገጽታና ዘርፈ ብዙ ምላሽ አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦቧል፡፡ ይህን ተክትሎ ለተነሱ ጥያቄዎችም በጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ ምላሽ ምላስ ተሰቶበታል፡፡
በወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዙሪያ ባሉ መልካም አጋጣሚዎችና ችግሮች ዙሪያ የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር አብርሃም ተከስተ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
ከሁሉም ክልሎች በተወከሉ ወጣቶች አማካኝነት ለሚነሱ ጥያቄዎችም በነገው ዕለት በኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ አማካኝነት ምላሽ እንደሚሰጥ የወጣው መርሀ ግብር ያስረዳል፡፡
የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም በፖሊሲዎችና ስትራቲጂዎች አፈጻጸም ዙሪያ ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡
በኮንፈርንሱ ላይ ከሶስት ሺ በላይ ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን የተለያዩ ወጣቶች ተሞክሮ የሚቀርብበት አውደ ርዕይም ተዘጋጅቷል፡፡
የወጣቶች የተሳትፎና ንቅናቄ ኮንፍረስ ቀደም ሲል በ1999 ዓ.ም ፣በ2001 ዓ፣ም እና በ2002 ዓ.ም በታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ አማካኝነት መካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡