በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ ወጣቱ ተገቢውን ሚና መጫወት አለበት-ወጣቶች

በአገሪቱ  የተለያዩ ክልሎች  የሚገኙ  የነገ  አገር ተረካቢ የሆኑት  ወጣቶች ላለፉት 25 ዓመታት  በአገሪቱ ሰፍኖ የቆየው ሰላምና መረጋጋት ለወደፊቱም በዘላቂነት  እንዲረጋጋጥ ለማስቻል ተገቢውን  ሚና  መጫወት እንዳለባቸው  የተለያዩ  የአገሪቱ  ወጣቶች  ገለጹ ። 

ዋኢማ ያነጋገራቸውና በተለያዩ የአገሪቱ  ክፍሎች  የሚኖሩ  ወጣቶች  እንደተናገሩት  በአገሪቱ  ሰፍኖ  የቆየውን  ሰላምና መረጋጋት  እንዲሁም  በመገንባት  ላይ  የሚገኘው  ዴሞክራሲና የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸውና ወደ የላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ለማድረግ ወጣቱ ትውልድ  የበኩሉን  ሚና መጫወት ይጠበቅበታል ብለዋል ።

የአዲስ  አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ካሳሁን ሙሉ እንደሚገልጸው ወጣቶች በኢኮኖሚ ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥያቄዎችን ለመንግሥት በማቅረብ  በህገመንግሥቱ  አግባብ  የመስተናገድ  መብት  እንዳላቸውም ተናግሯል ።    

በአገሪቱ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችንና ሌሎች ጥያቄዎችን  በዴሞክራሲያዊ አግባብ  በማቅረብ  በተለያዩ  መድረኮች  በመወያያት እንዲፈቱ  ወጣቱ  ትግል  ማድረግ እንደሚገባው የጠቆመው ወጣት ካሳሁን በ 21ኛው ክፍለ ዘመን የማይፈታ ችግር የለም ብሎ እንደሚያምን አመልክቷል ።

ሌላው የአማራ ክልል  ነዋሪ የሆነው ወጣት አንደበት ክንድዬ በበኩሉ እንደተናገረው  በአንዳንድ የአገሪቱ  አካባቢዎች የተከሰተው  ሁከት  እንደሚያሳስበው  በመጠቆም  ህብረ  ጥያቄ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ካሉም ከመንግሥት ጋር በአንድ  መድረክ በመገናኘትና በመቀራረብ  መግባባት ላይ  መድረስ ለወደፊቱ ይጠበቃል  ብሏል ።

የተለያዩ የዓለም አገራት  ፈጥነው ቀውስ  ውስጥ በመግባታቸው  ምክንያት  ሰላም እጅግ አስፈላጊ መሆኑ  በተለያዩ በቀውስ ውስጥ የሚገኙ  የዓለም ህዝቦች ተሞክሮ የሚያሳይ መሆኑን የጠቀሰው  ወጣት አንደበት   በስሜታዊነት   ከመነዳት  ይልቅ  ሁኔታዎችን   በሰከነ መንፈስ  ሁሉም እንዲያየው  ጠይቋል ።

የሺ አለም  አሰሙ   በአማራ ክልል   የደቡብ ጎንደር  ነዋሪ  እንደሆነች ገልጻ በአንዳንድ የአገሪቱ  አካባቢዎች  የተስተዋሉት  ሁከቶች  አገሪቱን አሁን  ከያዘችው  የልማትና  የዕድገት ጎዳና የሚጎትታት መሆኑን በመጠቆም  ችግሮች  በተከሰቱባቸው አካባቢዎች  የአስተዳደር  አካላት  እስከ ታችኛው የህብረተሰቡ አካላት ጋር በፍጥነት እንዲወያዩ በማድረግ  በአሉባልታ የሚነዙትን ወሬዎች በሙሉ ማስቀረት ይገባል ብላለች ።

ሌላዋ  በደቡብ ክልል  የወላይታ  ከተማ  ነዋሪ የሆነችው  ወጣት ፀጋ ነሽ ጥሩነህ በበኩሏ   በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ሁከት ዳግም እንዳይፈጠር ለማድረግ መንግሥት  ተከታታይ ውይይቶች ለማካሄድ ማቀዱ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን በመግለጽ  በአፋጣኝ  የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት  ከውጭ  የራሳቸውን ዓላማ  ለማሳካት የሚጥሩ ኃይሎች እንዳይጠቀሙበት ማድረግ ይገባል ብላለች ።