የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ ማግኘት ስለሚገባው ጥቅም ሰፋ ያለ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
ከ4ኛው ሀገር አቀፍ የወጣቶች ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎችን አቅርበዋል
ከጥያቄዎቹ መካከል ከኦሮሚያ ክልል ወጣቶች የተነሳው በህገ መንግስቱ የተደነገገውን የፊንፊና የልማት ጥያቄ በተመለከተ መንግስት ምን ለማድረግ አስቧል የሚለው ይገኝበታል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸውም ከዚህ ቀደም የተሰሩ ጥናቶችም አሉ፤ሁሉንም በአንድ ላይ በማቀናጀት ለሚንስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ ይቀርባል ብለዋል
በቀጣይም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት ላይ ሥራውን በሚጀምርበት ጊዜ ለምክር ቤቱ ቀርቦ በአዋጅ ደረጃ እንዲጸድቅ ይደረጋል ብለዋል።
መንግስት በየደረጃው የተለያዩ መድረኮችን በማመቻቸት ከህዝቡም ይሁን ከወጣቶች የሚቀርቡ የልማት እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው ያሉት አቶ ኃይለማርያም፥ የወጣቶች የተሳትፎ እና የንቅናቄ ኮንፈረንስም የወጣቶችን ጥያቄ ለመፍታት ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።
ኮንፈረንሱ ለጥቂት አመታት ተቋርጦ በመቆየቱ በመንግስት ስም ይቅርታ እጠይቃለሁም ነው ያሉት።
የወጣቶች የምክክር መድረኩ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።
ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው አራተኛው አገር አቀፍ የወጣቶች ኮንፍረንስም ወጣቶቹ ባለአምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል ።
ወጣቶቹ በመግለጫቸው መንግስት የወጣቱን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል።