የምክር ቤቱ ውሳኔዎች ቁልፍ ችግሮችና ክፍተቶችን የለዩ ናቸው-ቤጉህዴፓ

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ግንባር(ኢህአዴግ) ምክር ቤት ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ቁልፍ ችግሮችና ክፍተቶችን በአግባቡ የለዩ መሆናቸውን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ቤጉህዴፓ) አስታወቀ፡፡

በምክር ቤቱ የተላለፉት ውሳኔዎች ጥልቅ ውይይትና ግምገማ የተደረገባቸው መሆኑን የፓርቲው  ሊቀመንበር አምባሳደር ምስጋናው አድማሱ ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

የግንባሩ ምክር ቤት በ15 ዓመታት የተሃድሶ ጉዞ የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመፈተሸና በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡ በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለማከናወን እንደሚረዳ አምባሳደር ምስጋና ገልፀዋል፡፡

ምክር ቤቱ እንደ ድክመት ያነሳቸው ጉዳዮች አጋር ፓርቲውም ቀደም ሲል በክልል ደረጃ ባደረገው ድርጅታዊ ግምገማ ድክመት መሆናቸውን መለየቱን ነው ሊቀመንበሩ ያስረዱት፡፡

በቀጣይ ሊተኮርባቸውና በደንብ ሊሰራባቸው እንደሚገባ በምክር ቤቱ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች እውን እንዲሆኑ ቤጉህዴፓ እንደ አጋር ፓርቲ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚወጣ ሊቀመንበሩ አስረድተዋል፡፡

ችግሮችን በመፈተሽ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት የተቀመጡት አቅጣጫዎችም በደንብ ሊሰራባቸው እንደሚገባ ፓርቲው አስገንዝቧል፡፡ ውሳኔው አገሪቱ የተያያዘችውን የለውጥ ጎዳና አጠናክሮ ለመቀጠል የሚረዳ እንደሆነም ነው የተመለከተው፡፡

በክልል ደረጃ የ2008 ዓ.ም የመንግስትና የድርጅት ዓመታዊ አፈፃፀም መገምገሙን አምባሳደር ምስጋና አስታውሰዋል፡፡ በዚህም የተወሰኑ ክፍተቶች መለየታቸውን ነው አምባሳደር ምስጋናው የተገለፁት፡፡

በተለይም የጠባብነት አመለካከት ያለባቸው አንዳንድ አካላት በዚህ የተሳሳተ አስተሳሰብ ታጥረው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ እነዚህ አካላት ልማትን በማፋጠን የህዝቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ይልቅ ለራሳቸው ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው ታውቋል፡፡

በዚህ በኩል የታዩ ችግሮች በአፋጣኝ እንዲፈቱና ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲበጅላቸው እየተሰራ መሆኑን አምባሳር ምስጋናው አስረድተዋል፡፡ በጣም ጎልቶና ጫፍ የወጣ ችግር ባይኖርም የታዩትም በአፋጣኝ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ ይሰራል፡፡