በክልሉ በሚደረጉት ህዝባዊ መድረኮች ለሠላምና ልማት ግብዓት ተገኝቶባቸዋል

በአማራ ክልል በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከህብረተሰቡ ጋር የሚደረጉት ውይይቶች ሠላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ጥሩ ግብዓት መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

በውይይት መድረኮቹ ህብረተሰቡ ሠላሙን የሚያውኩ ዕኩይ ድርጊቶችን በማውገዝ የሚጠበቅበትን ለመወጣት መዘጋጀቱን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ለዋልታ አስታውቋል፡፡

በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በተከሰቱት ግጭቶች በሰው ህይወትና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳትና ውድመት ለማንም የማይበጅ መሆኑን አጥብቀው ማውገዛቸውን የፅህፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ መሰል ህገ ወጥ ድርጊቶች እንዳይከሰቱ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ለሠላምና ልማት እንደሚተጉ መግለፃቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

መንግስት የህብረተሰቡን ሠላም የመጠበቅ፣ የህግ የበላይነትና ህገመንግስቱን የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር በተያያዘ ከህዝብ ለሚነሱ ቅሬታዎችም አፋጣኝና ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጥ መናገራቸውን አቶ ንጉሡ ጠቁመዋል፡፡ በተለይም ለረጅም ጊዜ ሳይመለሱ በመቆየታቸው ቅሬታ እየፈጠሩ ያሉ ጥያቄዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡

ህብረተሰቡ በሰሜንና በደቡብ ጎንደር፤እንዲሁም በባህር ዳር ከተማ የተካሄደውን ሠላማዊ ሰልፍ ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት ማዘኑን በየመድረኮቹ መግለፁ ተመልክቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት ከህብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሾችን መስጠት እንዳለበት አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡ ከህብረተሰቡ ጋር የሚደረጉ ተመሳሳይ የውይይት መድረኮችም በየጊዜው ሊዘጋጁ እንደሚገባ መጠቆሙ ተመልክቷል፡፡

ከእነዚህም መካከል የገጠር መሬት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና መሰል የመልካም አስተዳደር እጥረት የሚስተዋሉባቸው ዘርፎች በውይይት መድረኮቹ ተነስተዋል፡፡

ከማንነትና ከወሰን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችም ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ምላሽ ቢሰጥባቸው መልካም እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

በመቻቻልና በመከባበር በኖሩ ህዝቦች መካከል በአንዳንድ አካላት ግጭትና መቃቃርን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረትም በዘለቄታዊነት ሊገታ እንደሚገባ በመድረኮቹ መጠቆማቸውን አቶ ንጉሡ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ከህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎችን በመያዝ ሠላምን ለማስፈን፤የመልካም አስተዳደር እንቅፋቶችን ለማስወገድ እና ልማትን ለማፋጠን ቆርጦ ተነስቷል ብለዋል- አቶ ንጉሡ፡፡

በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በሚካሄዱት የውይይት መድረኮች የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

በሰሜን ጎንደር የተወሰኑ ወረዳዎች፣ በደቡብ ጎንደር ሶስት ወረዳዎች እና በባህር ዳር ከተማ ሠላማዊ ሰልፍን ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት በሰው ላይ ሞትና የአካል ጉዳት፤እንዲሁም በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ ይታወቃል፡፡