ከ400 በላይ የጋምቤላ አመራሮች የአመራርነት ስልጠና እየወሰዱ ነው

በደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከ400 ለሚበልጡ የጋምቤላ ክልል አመራሮች የአመራርነት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑ ተመለከተ፡፡

ለአመራሮቹ እየተሰጠ ያለው ስልጠና የአመራነት ብቃታቸውን ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑን የደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የዳያስፖራ፣የሁለቱ ክልሎች ትብብር እና የፕሮቶኮል ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም አስራት ለዋልታ ገልፀዋል፡፡

ለአንድ ሺ አመራሮች ስልጠና ለመስጠት መታቀዱን አቶ ዘላለም ጠቁመው በመጀመሪያው ዙር 400 አመራሮች ስልጠናውን መውሰድ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ስልጠናውም በክልሉ ከሚገኘው የመለስ የአመራር ስልጠና ማዕከል ጋር በመተባበር ነው እየተሰጠ የሚገኘው፡፡

ቀሪዎቹ 600 አመራሮች በቀጣይ በሚዘጋጀው የስልጠና መርሀ ግብር መሰረት የሚሰለጥኑ ይሆናል፡፡ የአሁኑ ስልጠና ለሁለተኛ ጊዜ የተሰጠ መሆኑን አቶ ዘላለም ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በመንግስት ፖሊሲና የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ስልጠና መሰጠቱን አስገንዝበዋል፡፡ በአሁኑ በቅርቡ በጋምቤላ በተከሰተው ችግር ዙሪያ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰጥ ነው የገለፁት፡፡ ችግሮችን ለመፍታት ሊተገበሩ የሚገባቸው አቅጣጫዎችን በዝርዝር የማስጨበጥ ሥራም በስልጠናው ተካቷል፡፡

የፌዴራሊዝም ፅንሰ ሀሳቦች፣ የብሔረሰቦች እኩልነትና ነፃነትም በስልጠናው በስፋት የሚዳሰሱ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል፡፡ ስልጠናው በንድፈ ሀሳብና በተግባር የታገዘ እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡ የመስክ ጉብኝትም የስልጠናው አንድ አካል መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የስልጠናው ወጭ ሙሉ በሙሉ በደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ይሸፈናል ተብሏል፡፡

ሁለቱ ክልሎች በ1998 ዓ.ም ባደረጉት የትብብር ስምምነትን መሰረት ስልጠናው እየተሰጠ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ለ400 የጋምቤላ አመራሮች ስልጠና መሰጠቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ የተጀመረው የአመራሮች ስልጠና ጳጉሜ አምስት ቀን 2008 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡