ክልሎቹ የወሰን ችግርን በአፋጣኝ ለመፍታት መዘጋጀታቸውን ገለፁ

በአማራና በትግራይ ክልሎች ከወሰን ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ ለማበጀት መዘጋጀታቸውን ክልሎቹ ገለፁ፡፡

በሁለቱ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ( ህወሃት) እና ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ብአዴን) አመራሮች ተነጋግረው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚፈቱት የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ መግለፃቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቧል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳዳር እና የህወሃት ሊቀመንበር አቶ አባይ ወልዱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ፣ የትግራይ እና አማራ ህዝቦች በደም የተሳሰሩ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ትናንት ደርግን ለመጣል፤ ዛሬ ደግሞ ድህነትን ለማሸነፍ በጋራ የተዋጉና እየተዋጉ ያሉ ህዝቦች መሆናቸውን መናገራቸውንም ፋና በዘገባው አመልክቷል፡፡

የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ሀይሎች ሁለቱን ህዝቦች ለማለያያት የያዙት አጀንዳ እንደማይሳካም በአፅንዖት ገልፀዋል፡፡

ክልሎቹ ከወሰን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት በጋራ እንደሚሰሩም ነው የተመለከተው፡፡

ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ እስካሁን ለክልሉ መንግስት የቀረበ ጥያቄ እንደሌለም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል፡፡ ጥያቄ ከቀረበ የክልሉ መንግስት እንደሚያየው አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው የወሰን ችግር ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም መያዙን ለዋልታ ገልፀዋል፡፡

ሁለቱም ክልሎች ችግሩን ለመፍታት እስካሁን መዘግየታቸው ተገቢ አለመሆኑንም አቶ ንጉሡ ተናግረዋል፡፡ አሁን ግን ህወሃትና ብአዴን ችግሩን ለመፍታት በፍጥነት ወደ ተግባር ለመግባት መነሳታቸውን ገልፀዋል፡፡

ችግሮችን ተቀራርቦ ለመፍታትም ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡ ወሰን የማካለሉ ሥራ የሚከናወንባቸው ቦታዎች ዝርዝርና ስፋት ወደ ፊት ይገለፃል ብለዋል፡፡

የኢህአዴግ ምክር ቤት ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ በሁለቱ ክልሎች ከወሰን ማካለል ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን የህወሃትና የብአዴን አመራሮች ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ በአፋጣኝ እንዲፈቱ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡