ክልሎቹ የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ወሰናቸውን በሠላም ጠብቀዋል

የደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች እና የኦሮሚያ ክልሎች የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ወሰናቸውን ጠብቀው መቆየታቸው ተገለፀ፡፡

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የግጭት መንስዔ ይሆናሉ ተብለው በሚጠቀሱ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች የሁለቱን ክልሎች የጋራ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ለጉዳዩ መፍትሔ ማበጀቱን ተመልክተዋል ፡፡

የግጭት መንስዔ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉትን የሁለቱን ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ሁለቱ ክልሎች የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ባስቀመጡት የመፍትሔ አቅጣጫ ከስጋት የፀዳ አካባቢ ለመፍጠር መቻሉን የደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍቅሬ ግዛው ለዋልታ አስታውቋል ፡፡

በተለይም በሁለቱ ክልሎች በምዕራብ አርሲ በሚኖሩ ኦሮሞዎችና በሃዋሳ አቅራቢያ በሚኖሩ ወላይታዎች መካከል በአሸዋ ምክንያት ይነሳ የነበረውን ግጭት በመፍታት ረገድ ጥሩ ተሞክሮ መገኘቱን ያስረዳሉ፡፡

አቶ ፍቅሬ እንዳሉት የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ቀጥሎም ከሁለቱ ብሔሮች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎችም የግጭቱን መንስዔ በማጣራት ለጉዳዩ እልባት ለማግኘት የሚረዳ ውይይት አድርገዋል ፡፡

በዚሁም መሰረት  አሸዋውን የሁለቱም ክልል ነዋሪዎች በጋራ እንዲጠቀሙ ስምምነት ላይ በመድረስ በሠላም መኖር መቻላቸውን አብራርተዋል ፡፡

በተጨማሪም የክልሎቹ አዋሳኝ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ማህበረሰቦች ማህበራዊ ተቋማትን በጋራ የሚጠቀሙበት መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል ፡፡

በመሆኑም በአቅራቢያ የሚገኙ ጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶችን በጋራ ይጠቀማሉ ያሉት አቶ ፍቅሬ፤ ትምህርት ቤቶቹ በሁለቱም ማህበረሰቦች ቋንቋ እንዲያስተምሩ መደረጉን ገልጸዋል ፡፡

በዚህ መልኩ የተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት  ቀጣይነት ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በተለያየ ጊዜ በመገናኘት ውይይት ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልል መገናኛ ብዙኃንን ሬዲዮና ቴሌቪዥን በመጠቀም የሠላምን አስፈላጊነትና የግጭትን አስከፊነት በማጉላት ለህዝቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በስፋት እየተሰራ እንደሆነም ከኃላፊው ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡