የምክር ቤቱ ውሳኔ ተግባራዊ ይሆናል የሚል ሙሉ እምነት የለንም-ተቃዋሚ ፓርቲዎች

የኢህአዴግ ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ ተግባራዊ ይሆናል የሚል ሙሉ እምነት እንደሌላቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዋልታ ገለጹ ፡፡

ኢህአዴግ በተለያዩ ጊዜያት ውሳኔዎችን ቢያሳልፍም በተግባር ግን ማሳየት አለመቻሉን የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ ፕሬዚዳንት አቶ መሳፍንት ሽፈራው ገልጸዋል ፡፡

ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ ዘላቂ እርምጃ እንደሚወስድ በተደጋጋሚ ቢናገርም ጥፋተኛ የተባሉ አካላት ተለይተው ጥፋታቸው ለህዝብ ተገልፆ እርምጃ እንደማይወሰድ ፕሬዚዳንቱ ጨምረው አስረድተዋል፡፡

ኢህአዴግ ጥፋተኞች ላይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ሌላ ቦታ በተሻለ ደረጃ የመመደብ አካሄድን እንደሚከተል አቶ መሳፍንት አመልክተዋል፡፡

ውሳኔውም የዘገየና ችግሮች ሲፈጠሩ ፓርቲው የሚያደርገውን የተለመደ ሩጫ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ትግስቱ አወሉ የምክር ቤቱ ውሳኔዎች ተግባራዊ መሆናቸውን እንደሚጠራጠሩ ነው ያስታወቁት፡፡

ይህም ካለፉት የኢህአዴግ የእርምት እርምጃ ሂደቶች መገንዘባቸውን አስረድተዋል፡፡

ችግሮች ሲፈጠሩ በሌላ አካል ላይ በማላከክ ከተጠያቂነት ለመራቅ የሚደረግ ሙከራ እንደሆነም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በከፍተኛ የአመራርነት ቦታ ላይ ያሉትን አካላት ከመጠየቅ ይልቅ ታች ያሉ አመራሮችን ከኃላፊነት የማንሳት እርምጃ እንደሚወስድ አቶ ትግስቱ ጠቁመው ከዚህ ያለፈ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል አካሄድ አይከተልም ሲሉም ይገልጻሉ ፡፡

ውሳኔው መልካም ቢሆንም መሬት ወርዶ ተግባራዊ እስካልሆነ ድረስ የሚያመጣው ለውጥ የለም ባይ ናቸው፡፡

ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባም አቶ ትግስቱ ጠቁመው፤ ግንባሩ ጠበቅ ያለ እርምጃ ላለመውሰዱ ውስጣዊ የመተጋገል ሂደቱ ጠንካራ ስላልሆነ ሳይሆን አይቀርም የሚል ስጋት አላቸው፡፡

የኢትዮጵያ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዴኃግ) በበኩሉ የምክር ቤቱ ውሳኔዎች የዘገዩ መሆናቸውን አመልክቷል ፡፡

በመዘግየታቸውም አሁን የታዩት ችግሮች እንዲከሰቱ በር መክፈታቸውን የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ገረሡ ገሣ ገልጸዋል፡፡

ውሳኔዎች በተግባር ካለመፈፀማቸው በተጨማሪ  አፈፃፀሙ የተገላቢጦሽ የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩንም ሊቀ መንበሩ አመልክተዋል፡፡ ያጠፋን አመራር ሌላ ቦታ የመሾም አካሄድ መኖሩን በመጠቆም፡፡

 ‹‹የግንባሩ ምክር ቤት ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች የመተግበር ቁርጠኝነት ያለ አይመስለኝም›› የሚሉት ደግሞ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ ናቸው፡፡

ኢህአዴግ ችግሮች እንዳሉበት ቢገልፅም ተገቢውን የእርምት እርምጃ የመውሰድ የቁርጠኝነት ማነስ አለበት ይላሉ፡፡

በተለያዩ ጊዜያት እርምጃ ለመውሰድ እየገለፀ ተግባራዊ አለማድረጉ በህዝቡ ዘንድ ተአማኒትን አሳጥቶታል ብለዋል፡፡

አሁንም ቁርጠኛ አቋም ተይዞ ወደ ተግባር እስካልተገባ ድረስ ውጤቱ የተለየ አይደለም ብለዋል፡፡

ኢህአዴግ የተናገረውን በተግባር በማረጋገጥ ቁርጠኝነቱን ለህዝቡ ማሳየት እንዳለበትም ፓርቲዎቹ አሳስበዋል፡፡