አምስት ክልሎች ለ9 ሺህ 833 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረጉ

አምስት ክልሎች አዲሱን አመት ምክንያት በማድረግ ለ9 ሺህ 833 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጋቸውን አስታወቁ።

የትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ቤሻንጉል እና የአፋር ብሄራዊ ክልሎች ናቸው ምህረቱን ያደረጉት።

በዚህም መሰረት የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለ924 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አድርጓል።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል ደግሞ ለ5 ሺህ 463 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን ገልጿል።

የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልም፥ ለ3 ሺህ 300 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን አስታውቋል።

በተመሳሳይ የቤንሻንጉል ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፥ ለ111 የህግ ታራሚዎች አዲሱን አመት ምክንያት በማድረግ ይቅርታ ማድረጉን ገልጿል።

የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ፥ ለ35 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን ነው የገለጸው።

የየክልሎቹ ፀጥታና አስተዳደር ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊዎች እንዳሉት፥ ምህረት የተደረገላቸው ታራሚዎች ከቀላል ወራት እስከ እድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸውና የይቅርታ ህጉን ያሟሉ ናቸው፡፡

ታራሚዎቹ በቆይታቸው በጥፋታቸው የተጸጸቱና መልካም ስነ ምግባር በማሳየት ይቅርታ እንዲደረግላቸው ያመለከቱ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በይቅርታ ህጉ መሰረት በሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት የፈፀሙ፣ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የተፈረደባቸውና በሙስና የታሰሩ የህግ ታራሚዎች በይቅርታው እንዳልተካተቱም ጠቁመዋል።

ይቅርታ የተደረገላቸው የህግ ታራሚዎቹ ወደፊት፥ ከህብረተሰቡ ጋር በመግባባት በሰላም ሰርተው ለመለወጥ የበኩላቸውን እንዲወጡም ሃላፊዎቹ ጠይቀዋል።(ኤፍ ቢ ሲ)