ህዝቡ ለሠላምና ለደህንነት ዘብ እንዲቆም ፕሬዚዳንቱ አሳሰቡ

የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አዲስ ዓመትን በማስመልከት ለህዝቡ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሠላምና ደህንነት ዘብ መቆም አለበት፡፡

ህዝቡ ለዘመናት የቆየውን ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር ታሪካዊ ባህሉን በማጠናከር ለሠላም መስፈን ዘብ መቆም ይኖርበታል ብለዋል-ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ማዘናቸውን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመው ህዝቡ ጥያቄዎቹን በሠላማዊ መንገድ በማቅረብ ምላሽ እንዲሰጠው የማድረግ ባህልን ሊያዳብር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ችግሮችን በውይይት የመፍታት አካሄድን መከተል እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ልማትን ለማፋጠንና የዲሞክራሲ ጉዞውን ለማጠናከር ሠላምና መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ በአፅንዖት ገልፀዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ህዝቡ ከመልካም አስተዳደር እጥረት ጋር በተያያዘ ቅሬታዎችን እያቀረበ ይገኛል፡፡ ይህ በየትኛውም የዲሞክራሲ ሥርዓትን በሚከተሉ አገራት የሚስተዋል ጉዳይ ነው፡፡ህዝቡ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ መብቶቹን ተጠቅሞ ጥያቄ ማቅረቡም የዲሞክራሲ ሥርዓቱን መጎልበት የሚሳይ ነው፡፡

መንግስት ህዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች በማክበር አግባብነት አላቸው ብሎ ያመናቸውን ጥያቄዎች ከህዝቡ ጋር በመሆን ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በተከተለ መልኩ መፍትሄ እንደሚያፈላልግ ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል፡፡

‹‹መንግስት ራሱን በጥልቀት በማደስ፣ካለበት ብልሹ አሰራርና ጥገኝነት ተላቆ ያሉበትን ጉድለቶች በማረም ጥያቄዎቹን ለመመለስና የህዝቡን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል›› ብለዋል፡፡

ህዝቡ በህገ ወጥ መንገድ ከሚጓዙ አካላት ራሱን በማራቅ ለሠላምና ልማት እንዲተጋም ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል፡፡

ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር በማድረግ በንብረትና ሀብት ላይ ውድመትና ጉዳት እንዲደርስ የሚጥሩ አካላትን መንግስት ዝም ብሎ እንደማይመለከትም ፕሬዚዳንቱ በመልዕክታቸው አመልክተዋል፡፡

የአገሪቱን ህዳሴ ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች የገቡትን ቃል በአዲሱ ዓመት በተግባር እንዲያረጋግጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አዲስ ዓመትን በማስመልከትም የይቅርታ ቦርድ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ላቀረባቸው 707 የፌዴራል የህግ ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉ በፕሬዚዳንቱ ተገልጿል፡፡ ይቅርታ የተደረገላቸው የህግ ታራሚዎችም ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ የተሰጣቸውን ዕድል በመጠቀም ሠላማዊና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል፡፡

በአዲሱ ዓመት መላው ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ በመደጋገፍና በመግባባት፣ አንድነታቸውን በማጎልበት፣ የተሻለ ሠላምና መረጋጋት እንዲፈጠር የሚተጉበት እና ለድል የሚበቁበት ዓመት እንዲሆን ፕሬዚዳንቱ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡