ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው ዓመት በዲፕሎማሲው መስክ ስኬታማ ሆናለች

ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው ዓመት በዲፕሎማሲው መስክ ሰፊ ተቀባይነትና ትልቅ ስኬት ያስመዘገበችበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።  

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ በዲፕሎማሲው መስክ 2008 . የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክተው ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ሰላምና መረጋጋቷ፣የቀጣናውን ሰላም በማስጠበቅ በኩል እየተጫወተች ያለው ሚና ተቀባይነቷን ከፍ እንዲል አድርጎታል።

በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን በከፍተኛ ድምፅ መመረጧንም አንስተዋል።    

የተለያዩ ዓለም አገራት መሪዎች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው የአገሪቱ ተቀባይነት እየጎላ መምጣቱን ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል። 

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ፣የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ፣የእንግሊዝና የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትሮች እንዲሁም  የደቡብ ኮሪያዋ ፕሬዝዳንት አገሪቷን ከጎበኙት መሪዎች መካከል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተጠናቀቀው ዓመት ኢትዮጵያ ሦስት ኢምባሲዎችን በአልጄሪያ፣ሞሮኮና ኢንዶኔዥያ መክፈቷንም ተናግረዋል።  

ከተለያዩ አገራት ጋር ያላት ኢኮኖሚያዊ ትስስር ጠንካራ ሆኖ የዘለቀበት እንደነበርም አስታውሰዋል አቶ ሙሉጌታ። 

በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው መስክም ኢንቨስትመንትና ንግድን በማስፋፋት በኩል በበጀት ዓመቱ 47 ትላልቅ ኢንቨስተሮች ቅደመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት እንዲያደርጉ ታቅዶ 78 ጉብኝት አድርገዋል።  

በተመሳሳይ 1 ሺህ 21 መካከለኛና አነስተኛ ኢንቨስተሮች ቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ተወልደ 53 ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት ፍቃድ አውጥተው ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።   

እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ በዓመቱ በአገር ውስጥና በውጭ በተዘጋጁ 42 የቢዝነስ ፎረሞች ላይ ኢትዮጵያ ተሳትፋለች። 

150 በላይ  የንግድ ትርኢቶች ላይ በመሳተፍም አምራችና ገዥዎችን የማገናኘት ሥራ የተከናወነ ሲሆን ከጅቡቲ፣ኬኒያንና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋርም ቀጠናዊ የልማት ትስስር መፍጠር ተችሏል።

ከቱሪዝም አኳያ በተሰራው ሥራም 104 አስጎቢኚዎች ኢትዮጵያን እንደ አንድ የቱሪስት መዳረሻ ተቀብለው የማስተዋወቅ ስራ ሰርተዋል። 

ይህም ኢትዮጵያን የጎበኙ የቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር በማድረግና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም ከፍ እንዲል ማስቻሉን አመልክተዋል።  

በገጽታ ግንባታ በኩል የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በተለይ ከግድቡ ጋር በተያያዘ በግብጽና ሱዳን ጉብኝት በማድረግ ስኬታማ ውይይት ማካሄዱንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው ዓመት 560 የሚደርሱ የኮሚኒኬሽንና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ኢትዮጵያን ጎብኝተው የአገሪቱን መልካም ገጽታዎች  የሚያጎሉ ዘገባዎችን ለዓለም ያሰራጩበት አጋጣሚም ነበር። 

ከዳያስፖራ ተሳትፎ ጋር በተያያዘ 370 የምክክር መድረኮች መደረጋቸውን አስታውሰው 2009 . 400 በላይ የውይይት መድረኮችን ለማዘጋጀት መታቃዱንም ገልጸዋል። 

ደያስፖራው ለህዳሴው ግድብ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ በተሰራው ሥራ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር የቦንድ ሽያጭ ተከናውኗልም ብለዋል።

በመጨረሻም አዲሱ ዓመት ለመላው ኢትዮጵያዊያን የሰላም፣የልማትና ሰርቶ የመለወጥ እንዲሆን በመመኘት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።( ኢዜአ)