በአማራ ክልል ሠላማዊ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ተመለከተ

በአማራ ክልል ግጭት ተከስቶባቸው በነበሩ አንዳንድ አካባቢዎች ሠላማዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ህዝቡ ሠላሙን ለማስጠበቅና ወደ ግጭት የሚመሩ ጉዳዮችን ለመከላከልና ለመመከት ባደረገው ጥረት ሠላም መስፈኑን የፅህፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለዋልታ ገልፀዋል፡፡

ቀደም ሲል ግጭቱን ተከትሎ አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ የተለያዩ ተቋማት አሁን ሙሉ በሙሉ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ነው አቶ ንጉሡ  የተናገሩት፡፡

ወቅቱ የበዓል ጊዜ በመሆኑም በተለይም በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማትና የትራንስፖር አገልግሎት በቀደመው ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡ ስለሆነም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ህዝቡ እንዳይቸገር በማድረግ በኩል ጥሩ ደረጃ ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋምና ቤት የወደመባቸውንም ለመስራት ቃል እየገባና ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ ነው የተመለከተው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ህብረተሰቡ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ንብረቶችን ባለበት ሁኔታ በመጠበቅ ድጋፍና አጋርነቱን እያሰየ ነው ብለዋል፡፡

በሠላምና ልማት ዙሪያ ከህብረተሰቡ ጋር የሚደረገው ውይይትና ምክክር አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን የህዝቦችን ትስስርና አንድነት የማጠናከር ተግባራትን ያከናውናል ተብሏል፡፡ ተከስቶ በነበረው ግጭት የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖችን የማቋቋምና የመደግፍ ሥራ ይሰራል፡፡

የክልሉ መንግስትና ህዝብ አሁን ያለውን ሰላማዊ ሁኔታ ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል ከተከሰተው ችግርም ትምህርቶችን በመውሰድ ወደ ተግባር መገባቱን አቶ ንጉስ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ለአማራ ህዝብና ለመላው ኢትዮጵያውያን አዲሱ ዓመት የሠላም፣ የብልፅግና፣የልማትና ሁሉም ያቀደው የሚሳካበት እንዲሆን አቶ ንጉሡ በክልሉ መንግስት ስም መልካም ምኞታቸውን አስተላፈዋል፡፡