የማህበራዊ ሚዲያዎች አጠቃቀም ኃላፊነት የተሞላበት መሆን አለበት – ምሁራን

ማንኛውም ዜጋ የማህበራዊ ሚዲያዎችን ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ መጠቀም   እንደሚገባው  የተለያዩ   ምሁራን  አመለከቱ ።

በአሁኑ ወቅት በታዳጊ አገራት የማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚዎች  ቁጥር በከፍተኛ  ቁጥር   እያደገ መምጣቱን  የጠቆሙት  ምሁራኑ የማህበራዊ ሚዲያዎች  በማህበረሰብ ላይ በጎ ተጽዕኖ  ማሳደር  እንደሚችሉ  ሁሉ አስፈላጊ ጥንቃቄዎች ካልተደረጉ አሉታዊ ተጽዕኖን  የማሳደር አቅም እንዳላቸው  ገልጸዋል ።

በአዲስ  አበባ ዩኒቨርስቲ  የፓለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አቶ ዳር እስከዳር ታዬ ለዋኢማ በሠጡት አስተያየት እንደገለጹት በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚወጡ መረጃዎች በሙሉ እውነትም ናቸው ማለት እንደማይቻልና ማንኛውም ተጠቃሚ የሚያገኛቸው መረጃዎች ትክክለኝነትን  ማጣራት ይጠበቅበታል ብለዋል ።

በማህበራዊ ሚዲያዎች  መረጃዎች የትኛውም ግለሰብ በየትኛው ቦታ በመሆን ሊያሠራጨው እንደሚችል  የሚያስረዱት አቶ ዳርእስከዳር በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያስከትሉትን አሉታዊ ተጽዕኖን ለመቀነስ  ከተፈለገ በዋና ዋና የመገናኛ ብዙሃን በመጠቀም ለማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍል በሚፈለገው ፍጥነት መረጃ በማቅረብ በኩል ይበልጥ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል ።

በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በህብረተሰቡ ውስጥ ቅራኔንና ግጭትን የሚቀሰቅሱ መረጃዎች   የሚሠራጩበት ሁኔታዎች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ዳር እስከዳር ብሔር ተኮር የሆኑና  ከፋፋይ ከሆኑ መረጃዎች ህብረተሰቡ እራሱን መከላከል እንዳለበት አስተያየታቸውን ሠጥተዋል ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬንሽን ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ አቤል አዳሙ በበኩላቸው  በማህበራዊ ሚዲያዎች  በፍጥነት  የሚለቀቁ  መረጃዎችን  በተለይ   የተማረው የህብረተሰብ ክፍል የተለየዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ሊያረጋግጠው እንደሚገባው ተናግረዋል ።

ሌላው በማህበራዊ ሚዲያዎች ፖለቲካው፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ትችቶችን  በማቅረብ  በአንድ አገር ውስጥ ሊስተካካሉ  ስለሚገባቸውን  ሁኔታዎች  ጥቆማ በመሥጠት  መንግሥት  መልካም አስተዳደርን እንዲያሰፍን፣ ይበልጥ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማትን እንዲያመጣ በማድረግ ልክ እንደ አንድ በጎ አስተዋጽኦ ማድረጊያ መሣሪያዎች አድርጎ መጠቀም  እንደሚቻል አቶ  አቤል አብራርተዋል ።

በማህበራዊ ሚዲያዎች ማንኛውም  መረጃ  ያለምንም ገደብ ሊሠራጩ የሚችሉበት መንገድ እንደመሆኑን መጠን  አሉባልታ አዘል  መረጃዎችም  ጭምር  የሚወጡበት በመሆኑ የተወሰነ መቆጣጣሪያ ዘዴ  ቢኖረም  መልካም  ሊሆንም እንደሚችል አቶ አቤል አስረድተዋል ።