ለሰላም፣  ልማትና ዴሞክራሲ መረጋገጥ የፌደራል ስርለዓቱ ፋይዳ የጎላ ነው፤ ሚኒስትር ካሳ ተክለብርሃን  

የፌዴራል ስርዓቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የእኩልነት፣ የሰላምና የልማት  ጥያቄዎችን  የመለሰና በቀደሙት ስርዓታት የነበሩ  ሌሎች  ስር የሰደዱ ችግሮችን መፍታቱን የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ።

 

ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተክለብርሃን በተለይ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት የፌዴራል ስርዓቱ  ቀጣይነት ያለው ልማትን ከማረጋገጥ፣ ዘላቂ ሰላምን ከማስፈንና የዴሞክራሲ ስርዓትን ከመገንባት አንጻር ባለፉት ሁለት  አስርት ዓመታት የጎላ ፋይዳ ነበረው።

 

የሕዝቦች  የብሄር ጭቆናን አስወግዷል ፣ የሃይማኖት ነጻነትን አረጋግጧል፣ ሰላምና መረጋጋትን አስፍኗል፣   ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን አረጋግጧል፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን መሰረት እንዲይዝ አድርጓል ብለዋል።

 

አገሪቱ በምስራቅ አፍሪካ የሰላም ደሴት እንድትሆን አስችላል ያሉት አቶ ካሳ አልፎ አልፎ የሚታዩ ትናንሽ ግጭቶች ቢኖሩም በመሰረታዊነት የአገራችን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሚያውኩ አይደሉም ብለዋል።

 

አቶ ካሳ አያይዘውም የህዝብ  የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነት ያረጋገጠ ስርዓት መገንባቱን ጠቁመው ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የአገሪቱ ዴሞክራሲ  እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

 

ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንድያስተዳድሩና የአካባቢያቸውን ጸጋ ተጠቅመው አካባቢያቸውን እንዲያለሙ ቋንቋቸውንና ባህላችውን እንዲያበለጽጉ በማንነታቸው ኮርተው የጋራ አገራቸውን እንዲገነቡ የጎላ ሚና እንዳለው ም አቶ ካሳ ገልጸዋል።

 

እንደ አቶ ካሳ ገለጻ ህዝቦች በአካባቢው ልማት፣ ዴሞክራሲ ግንባታና ሰላም በባለቤትነት ስሜት  በሰፊው እንዲሳተፍ አግዟል።  ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት የነበረው የጤና፣ ትምህርትና መሰረተ ልማት ዓለምን ባስደመመ መልክ መቀየሩም  የዚሁ   ውጤት መሆኑን አስምረውበታል።

 

የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት የሆኑት ሁሉም የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የትምህርት ማዕድ ተቋዳሽ ለማድረግ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከ30 ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውንም አቶ ካሳ ተናግረዋል።

 

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት ሁነኛ መለያ ነው ያሉት ሚኒስትሩ እያንዳንዱ አካባቢ ያለውን ጸጋ ለይቶ ልማትን ለማፋጠን እንዲተጋ አመች ሁኔታና አስተሳሰብ ፈጥሯል ብለዋል።  

 

ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑ የዓለማችን አገራት የፌዴራል ስርዓት እንደሚከተሉ አስታውሰው የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት ብሔሮች፣ ብሔሰቦችና ሕዝቦች በቀጥታ የሚወከሉበትና ፍትሃዊነቱን ለማረጋገጥ ደግሞ በአንድ ሚሊዮን ህዝብ አንድ ተወካይ የሚሰይምበት   መሆኑ ከሌሎች አገራት ይለየዋል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት ማንነትን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት በመያዙም ከሌሎች አገራት የፌዴራል ስርዓት መለየቱን ጠቁመው ይህ ቋንቋን ለመጠቀምና ባህልን ለማሳደግ የጎላ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።

 

የፌዴራል ስርዓቱን ፋይዳ ለሕብረተሰቡ በተለይ ለወጣቱ በማሳወቅ ደረጃ የተፈጠረው ክፍተት እንደ አንድ ተግዳሮች መውሰድ ይቻላል ያሉት ሚኒስተሩ በዚህ ምክንያት በሕገመንግስቱ የተመለሱ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ሲቀርብ ይስተዋላል ነው ያሉት።

 

እኩል የመልማት እድል ለሁሉም ክልሎች ያጎናጸፈ ቢሆንም በሙያተኛ አቅምና በተነሳሽነት  ማነስ  የተነሳ ክልሎች በእኩል ደረጃ መልማት አለመቻላቸው ሌላው የስርዓቱ ተግዳሮት መሆኑን  ጠቁመው የመንግስት አካላት ስልጣንን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጠቀምም  ሌላው የጎላ ችግር እንደሆነ ገልጸዋል።

 

አቶ ካሳ አያይዘውም የፌዴራል ስርዓቱ መሰረት በመገንባቱ፣ የአገሪቱ ሃብት እያደገ በመምጣቱ፣ በርካታ ዜጎች ከድህነት እየወጡ በመምጣታቸው፣ የማህበራዊ ተቋማት በመስፋፋት ላይ በመሆናቸውና ይህንን ተከትሎ የህዝብ ተጠቃሚነት እያደገ በመምጣቱ በፌዴራል ስርዓቱ የተደቀኑት ተግዳራቶችን ማስወገድ እንደሚቻል አስምረውበታል።