ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ የፀጥታ ኃይሉ የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር አለበት – አቶ ካሳ ተክለብርሃን

በአገሪቱ   የሚገኙ   የፀጥታ የአስተዳደር አካላት  ህገ መንግሥታዊ  ሥርዓቱን  በማስጠበቅ  ረገድ እየተወጣ  የሚገኘውን ሚና ለወደፊቱም አጠናክሮ  መቀጠል እንደሚገባው የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር ልማት ሚንስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃን  አስታወቁ ።  

የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለተውጣጡ የፀጥታ አስተዳደር አካላት እየተሠጠ ባለው ሥልጠና ላይ እንደተናገሩት የአገሪቱ  የፀጥታ አካላት ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማስከበር ሚናውን ይበልጥ ማጎልበት ይኖርበታል ።

ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ማስጠበቅ ማለት በአገሪቱ ሰፍኖ የቆየውን ሰላምና መረጋጋት     እንዲሁም  የተጀመሩ የልማት  ሥራዎችን ማስቀጠል ነው ያሉት አቶ ካሳ  ለአገር ሰላም   ዘብ  ሆኖ የቆየው  የፀጥታ  ኃይል አሁንም ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በብቃት እየመከተ ይገኛል ብለዋል።

የአገሪቱ ህገመንግሥት ትልልቅ ጥያቄዎች  የመለሰ መሆኑን የጠቆሙት  አቶ  ካሳ ጉድለቶች  በሚኖሩበት ጊዜም ህገመንግሥቱ  ችግሮች የሚታረሙበትን ሁኔታ ማስቀመጡንና  የፀጥታ አካላትን ጨምሮ ሁሉም  የህብረተሰቡ ሊገነዘበው እንደሚገባው ገልጸዋል ።

የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር ለወደፊቱ ከሐይማኖት አባቶች ፣ ከወጣቶች ፣ ከምሁራንና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች  ጋር የውይይት  መድረኮችን በማዘጋጀት  የተፈጠሩ ግጭቶች ላይ  መፍትሔ ለማምጣት ይሠራል ብለዋል ።

የፌደራል ሥርዓቱ ቋሚ ጠላት የሆነው የሚገኙ በተለይም የውጭ ኃይሎች እንዳሉ የሚገልጹት  አቶ ካሳ  ወጣቶችን እንደ መሣሪያ በመጠቀም  እንቅስቃሴዎችን የሚያድርጉበት  ሁኔታ እንዳለም ተናግረዋል ።

ሰላም ወዳዱ  ህብረተሰብ በአገሪቱ  ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲቀጥል የሚፈልግ በመሆኑ ችግሮች  በሚያጋጥሙበት  ጊዜ የአገሪቱ ህገ መንግሥት  ድንጋጌዎች በሚፈቅደው  መሠረት የህዝቡን ሰላምና  አንድነት  በሚያስጠብቅ መልኩ የፀጥታ አካላት ፣ የአስተዳደር አካላትና ህብረተሰቡ ተቀናጅተው  የሚፈቱበትን ሁኔታ እንደሚያስፈልግ አቶ ካሳ አስረድተዋል ።