ህብረተሰቡ ሰላምን ለማስጠበቅ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ዘብ መቆም አለበት

ህብረተሰቡ በአገሪቱ ሰፍኖ  የቆየውን  ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን  ለማስቀጠልና የተጀመሩ  የልማት ሥራዎች  እንዲቀጥሉ  ለማድረግ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን  መቆም  አለበት ።

በተለያዩ  የአገሪቱ  ክፍሎች በፀጥታ ሥራ ላይ  የተሠማሩ  ዜጎች  ለዋኢማ  አስተያየታቸውን እንደገለጹት በአገሪቱ ሰፍኖ የቆየውን ሰላምና መረጋጋትን እንዲቀጥል ለማድረግና በተከታታይ በአገሪቱ እየተመዘገበ የሚገኘው የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲቀጥል ለማስቻል  ህብረተሰቡ የሰላም ዘብ ሆኖ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር መሥራት ይገባዋል ብለዋል ።

ከአማራ  ክልል  ሃብሮ ወረዳ  ፓሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ  የሆነው ዋና ኢንስፔክተር ጥላሁን  ታደሰ እንደሚናገረው  በአንድ አገር  የሰላም አስፈላጊነት የሚታወቀው  ሰላም ከእጅ ከወጣ  በኋላ ሊሆን ይችላል ነገር ግን በፀረ ሰላም ኃይሎች አማካኝነት  በሚናፈሱ  ወሬዎች የሚፈጠሩ ችግሮችን  በመፍታት  ረገድ  ህብረተሰቡ  ከፀጥታ ኃይሎችና አስተዳደር አካላት ጋር ይበልጥ   ተባብሮ መሥራት ይኖርበታል ።

በአማራ ክልል የዋግምህራ ዞን የፀጥታ ኃላፊ የሆነው ብርሃኑ አበበ በበኩሉ በአገሪቱ ተግባራዊ የተደረገው  የፌደራል ሥርዓቱ አገሪቱን  ከመበታታን አደጋ የታደጋት መሆኑንና ማንኛውም የፀጥታ  አካል  በየትኛውም አካባቢ ግጭት ቢከሰት እንኳን የህገ መንግሥቱን መሠረታዊ መርሆች በመከተል ከህብረተሰቡ  ጋር በመሆን ሊፈታ ይገባል ብሏል።

የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የመብት ጥያቄ  በሚያቀርበበት ወቅት የፀጥታ ኃይሉ የህዝብ አገልጋይ  እንደመሆኑ መጠን በተቀመጠው የህግ አግባብ ማስተናገድ አለበት ያለው ብርሃኑ ህብረተሰቡም ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን ለሰላም መጠበቅ በአንድነት መሥራት እንደሚጠበቅበት ተናግሯል ።

በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን የጀሌ ጥሙጋ ወረዳ የፀጥታ ኃላፊ የሆነው ኢንስፔክተር ዳዊት ጳውሎስ በሠጡት አስተያየት በአንድ ቦታ ግጭት ከመከሰቱ በፊት የተለያዩ ሥራዎች መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁሞ በፀጥታ ሥራው ላይ ህብረተሰቡን ማሳተፍ  መልካም  ውጤትን ለማግኘት እንደሚረዳ ገልጿል ።

በምዕራብ ሐረረጌ ግራዋ ወረዳ የፀጥታ ምክትል ኃላፊ የሆነው መሐመድ ሸሪፍ እንደሚገልጸው አንድ አካባቢም ሆነ አገር ሰላም  መከበር  ተጠቃሚው ህብረተሰብ  በመሆኑ ለየትኛውም  የፀጥታ ችግር ህብረተሰቡ ከአስተዳደርና ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት  ዘላቂ መፍትሔዎችን ማምጣት ይችላሉ ብሎ እንደሚያምን አመልክቷል ።