በጥልቀት የመታደስ ሂደቱ መልካም አስተዳደርን በማስፈን ህብረተሰቡን የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋል – ደኢህዴን

በጥልቀት የመታደስ ሂደቱ መልካም አስተዳደርን በማስፈን በዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ህብረተሰቡን የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ አስታወቀ።

ድርጅቱ በጥልቀት የመታደስ ሂደቱን እስከታችኛው መዋቅር ለማካሄድ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ትናንት በሠጡት መግለጫ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያስቀመጣቸውን ውሳኔዎች መነሻ በማድረግ ማዕከላዊ ኮሚቴው በጥልቀት የመታደስ መድረክ አካሂዷል፡፡

ያለፉት 15 ዓመታት የተሃድሶ ጉዞና ክልሉ አሁን የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ማዕከል በማድረግ በሂደቱ የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎች፣ ተግዳሮዎችና ወቅታዊ የሆኑ ቁልፍ ችግሮች በጥልቀት መገምገሙን ገልፀዋል፡፡

ከ15 ዓመታት በፊት የተሃድሶ ጉዞው ሲጀመር የሃገሪቱም ሆነ የክልሉ ቁልፍ ችግር የሆነውን ድህነት ለማሸነፍ በመሰራቱ በገጠር የአርሶ አደሩን ምርታማነት የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ የተከናወነው ተግባር ውጤታማ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የክልሉ አርሶ አደር የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከራስ ገቢ ባለፈ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ቡናና ሰሊጥን ጨምሮ ሌሎች ሰብሎችን በማምረት በገበያ የሚመራ አርሶ አደር መፈጠሩን ነው ያነሱት። 

በአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ማዕቀፍ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው መላውን ህብረተሰብ አስተባብሮ በመስራት አምስት ከመቶ የነበረው የክልሉ ደን ሽፋን ወደ 20 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡

በከተሞች ድህነትን ለማስወገድ የተቀመጡ የልማት ስትራቴጂዎች ሴቶች፣ ወጣቶችና ስራ አጦችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ከተሞች የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ ሆነው ገጽታቸው እንዲቀየር ማስቻሉንም አብራርተዋል።

በክልሉ በኢኮኖሚ ልማት የታየው ውጤት በማህበራዊ ልማትም የተመዘገቡ ናቸው ያሉት ኃላፊው፥ በትምህርት፣ በጤና እና በመሰረተ ልማት ዘርፍ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በአጠቃላይ ያለፉት 15 ዓመታት ጉዞ በክልሉ በሁሉም ዘርፍ እድገት ማምጣቱንና ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሆነበት ዓመት መሆኑን ማእከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡

በየደረጃው የተመዘገቡ ውጤቶች ከህዝቡ ፍላጎትና ከተቀመጠው አቅጣጫ አንጻር በቂ ያለመሆኑን የገመገመው ማዕከላዊ ኮሚቴው ፈጥኖ መታረም የሚገባ ጉድለት እንዳለ መታየቱን ጠቅሰዋል፡፡

በጥልቀት የመታደስ መድረኩ በጉድለት ካነሳቸው ነጥቦች መካከል አሁንም ከድህነት ያልወጡ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ በመስራት የፈጣን እድገቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

የልማትና የእድገት ፖሊሲው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በተደራጀ መልክ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ጉድለት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ወጣቶችን አሁን ካለው በተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ በዘርፉ የሚታየውን ማነቆ በመፍታት ሃገሪቱን የኢንዱስትሪ ማዕከል የሚያደርጉ ወጣቶችን ለማፍራት አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡

በየደረጃው በድርጅትና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያለው አመራር ለስልጣን ያለው አመለካከትና ተግባራዊ አፈጻጸም በጥልቀት የመታደስ መድረኩ ትኩረት የተሰጠበት ነው፡፡

ከህዝብ የተሰጠውን ስልጣን ህዝብን ከማገልገል ይልቅ ለግል ጥቅማቸው በመጠቀማቸው ጠባብነትና ጎሰኝነትን የፈጠሩ አመራሮች በመኖራቸው ማዕከላዊ ኮሚቴው እነዚህን ችግሮች ለማቃለል አቋም መያዙን ተናግረዋል፡፡

በመልካም አስተዳደር ንቅናቄው ለውጥ መመዝገቡን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት የሚሰራበት የተሃድሶ መድረክ እንደነበረ አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ሂደት ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመሆን የድርጅቱን በጥልቀት የመታደስ ሂደት ሊያግዝ እንደሚገባ በማሳሰብ ድርጅቱም በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች መድረኩን ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ውስጥ ያለውን ሰላምና መረጋጋት ለማስቀጠል ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡(ኢዜአ)