ኦህዴድ የጀመረውን ጥልቅ ተሃድሶ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ የጀመረውን ጥልቅ ተሃድሶ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ወሳኝ ወቅት ላይ መሆኑን የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴው አስታወቀ።

የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴው በላከው መግለጫ ኦህዴድ  ከመስከረም 4  እስከ 11 ቀን 2009 ድረስ በአዳማ ከተማ አባገዳ አዳራሽ በካሄደው ጥልቅ የተሃድሶ ግምገማ ውሳኔዎችን ማሳለፉን  ገልጿል።

በኦህዴድ አመራር በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 15 ዓመታት የተሳኩ ምዕራፎች ብሎ ከወሳዳቸው  ዘርፎች መካከል ህዝቡን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ የተደረገው ዘመቻና የተገኘው ስኬት በገጠርና በከተሞች ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ማዕከላዊ ኮሚቴው አመልክቷል።

የአርሶ አደሩን  ምርታማነት ለማሳደግ የተሟላ የግብርና ኤክስቴሽን ድጋፍ በመስጠትና በማስፋፋት እንዲሁም አዳዲስና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ድህነትን ከገጠር በሂደት መቀነስ መቻሉንም መግለጫው ጠቅሷል።

ድርጅቱ የክልሉን አርሶ አደሮች የአኗኗር ዘይቤ ለመለወጥ የተጓዘበት መንገድ ረጅም መሆኑን የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴው አመልክቷል።

የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲውና ስትራቴጂው በድህነት ቅነሳ ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲጫወት ርብርብ ላደረጉ አርሶና ርብቶ አደሮች፣ የልማት ጣቢያ ሠራተኞችና ባለሙያዎች ማዕከላዊ ኮሚቴው ምስጋና አቅርቧል።

የአርብቶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ  የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድ፣ የመስኖና የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማዘመን በተደረገው ጥረት በማህበረሰቡ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማረጋገጡንም አመልክተዋል።

በድርጅቱ አመራር የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ በማድረግና አሰጣጡን በማሻሻል የእናቶችንና የህፃናት ሞትን ለመቀነስ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት በተደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል። 

በጤናው ዘርፍ ለመጣው መሰረታዊ ለውጥ መላው የኦሮሞ ህዝብ፣ በየደረጃው የሚገኙ ባላሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከድርጅቱ ጎን ሆነው  ከፍተኛ ርብርብ  ማድረጋቸውንም መግለጫው አመልክቷል።

የገጠር መንገድና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ተደራሽነት፣ መብራትና የመገናኛ አውታሮችን  በማስፋፋት ረገድ የመጣው መሰረታዊ ለውጥ የኦህዴድ የአመራር ሰጪነት ውጤት መሆኑንም መግለጫው  አመልክቷል።

በአፈፃፀም ውስጥ የሚታዩ ችግሮች እንዳሉ ሆነው በሁሉም መስኮች የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች የአገሪቷን ታሪክ የለወጡ መሆናቸውን ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው አስታውቋል።

የገጠርና የከተማውን ህብረተሰብ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ለማስተሳሰር በተደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት ከተሞችን ለኑሮ አመች እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ የስራ አጥነትንና ድህነትን ደረጃ በደረጃ  በማቃለል ረገድ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውንም አመልክቷል።

ኦህዴድ ባለፉት ዓመታት ባስመዘገባቸው ስኬቶች የሚኮራ ሳይሆን  ለህዝቦች የላቀ ተጠቃሚነት በሙሉ አቅሙ እየተጋ ያለ የሕዝብ ድርጅት መሆኑንም መግለጫው ጠቅሷል።

ዲሞክራሲን ባህል ያደረገ የጠራ መስመር በማንገብ የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከመሰረቱ ያነገበ መሪ ድርጅት ነው ያለው የማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ ልማትና ዲሞከራሲን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር በሚደረገው ጉዞ ውስጥ መላው የኦሮሞ ህዝብ ድጋፍና ወገንተኝነት እንዳይለየውም ጠይቋል።

በረጅም የተሃድሶ ጉዞ ውስጥ ባለፉት 15 ዓመታት ያጋጠሙ ችግሮች የኦህዴድ የትግል መስመር ማጠናክሪያ መሆናቸውንም መግለጫው ጠቅሷል።

በህዝብ ወገንተኝነትና አብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመርን  ይዘን እየተጓዝን ባለንበት ወቅት በውስጣችን በተፈጠረው ግለኝነት ከህዝብ የተሰጠ ስልጣንን ለራስ መበልፀጊያና መጠቀሚያ በማድረግ የተፈጠረውን ችግር ከህዝቡ ጋር ተቀናጅተን ተሃድሶዋችንን እናሳካለንም ብሏል።

ኦህዴድ ከህዝቡ የሚነሱትን ሁሉን አቀፍ ጥያቄዎች በመገምገምና የታዩ ችግሮችን በመለየት  የማስተካከያ እርምጃዎችን የሚወስድ ድርጅት መሆኑን ህዝቡ ይገነዘባልም ነው ያለው ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው።

ድርጅቱ አሁንም ህዝቡ ያነሳቸውን ቅሬታዎች በጥልቀት በመመዘን አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኑን ለማረጋገጥም ባለፈው ለተፈጠረው ክፍተት ህዝቡን ይቅርታ በመጠየቅ መልካም አስተዳደርና ልማትን ለማስቀጠል  እየሰራ መሆኑን ገልጧል።

በገጠርና በከተሞች ለልማትና ለለውጥ የተዘጋጀ ጠያቂ ማህበረሰብ መፍጠር ተቸሏል ያለው ማዕከላዊ ኮሚቴው፣ የስራ አጥነት ችግርን በህዝቡ የነቃ ተሳትፎና በራሱ ትግል ደረጃ በደረጃ ለማቃለል  ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።

በመላው የኦሮሞ ህዝብ ተሳትፎ የገጠሙትን የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የማስፈፀም አቅም ውስንነት፣ የልማትና የመብት ጥያቄዎችን ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል።

የተፈጠረውን ውስጣዊ ችግር የፀረ ሰላም ኃይሎች እንደ መሳሪያ በመጠቀም ባናፈሱት ፕሮፓጋንዳ በክልሉ ለጠፋው የሰው ህይወትና ለወደመው ንብረት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ማዕከላዊ ኮሚቴው ገልጿል።

ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድና የተገኙትን ሁሉን አቀፍ ድሎች ወደኋላ ለመመለስ የሚጥሩትን ህዝቡ እንዲታገላቸው ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪ ያቀርባል።

የአፍራሽ ኃይሎች ተልዕኮ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል በመናድ ሀገርን መበታተን ነው ያለው ማዕከላዊ ኮሚቴው፣ በክልሉ  የሰፈነውን አስተማማኝ ሰላም በፅኑ መሰረት ላይ ለማስቀጠል ትግሉ የሚጠይቀውን መስዕዋትነት ሁሉ በመክፈል እኩይ ዓላማቸውን ለማምከን ድርጅቱ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል፣ ሰፊው የአሮሞ ህዝብም ከጎኑ እንዲቆም ጠይቋል።

በአቋራጭ መንገድ ወደ ስልጣን ለመምጣት የሚንቀሳቀሱ አፍራሽ ኃይሎች መቼም ቢሆን የማይሳካላቸው መሆኑን በመገንዘብ ህዝቡ በፅናት እንዲታገላቸው ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግላጫው  አመልክቷል።

ኦህዴድ የጀመረውን ጥልቅ ተሃድሶ ውጤታማ ለማድረግና ከህዝቡ የተነሳውን የልማት፣ የፍትህና የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን  ለመመለስና አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን የሚያስችሉ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው አመልክቷል/ኢዜአ/ ።