በ1 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነባው የቱሪስት መዳረሻ ማዕከል በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችን ለጎብኝዎች ለማስተዋወቅ፥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ይገልጻል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ገብረጻድቅ ሀጎስ ማዕከሉ በከተማዋ የሚመጡ ጎብኝዎች የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ያደርጋል ይላሉ።
በ114 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው የቱሪስት መዳረሻ ማዕከል መሉ ወጪው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚሸፈን ሲሆን፥ የግንባታ እና ዲዛይን ጥናቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከ 2 ዓመት በፊት ተጠናቋል።
ባህል ማዕከሉ የብሄር ብሄረሰቦችን አለባበስና የአለባበስ ስርዓት፣ ውዝዋዜና የተለያዩ ባህላዊ የጋብቻ ስነ ስርዓቶችን ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ ለጎብኝዎች የሚቀርቡባቸው ህንፃዎችንም ያካተተ ነው።
ማዕከሉ የተለያዩ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ ከእንጨት የተሰሩ የኢትዮጵያውያንን ባህል የሚያንፀባርቁ ቁሳቁስ እና ጌጣጌጦች፥ ለሽያጭ እና ለእይታ የሚቀርቡባቸው ህንጻዎችንም ያካትታል ተብሏል።
በተጨማሪም ጉብኝዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያካሂዱባቸው የባህል እና ዘመናዊ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችም በማዕከሉ ተካተዋል።
ይህ መሆኑም የሀገሪቱን ገጽታ በተሻለ መንገድ ለማስተዋወቅ ይረዳል ነው ያሉት የቢሮ ኃላፊው አቶ ገብረጻድቅ።
መዳረሻ ማዕከሉን በልዩ ትኩረት ለመምራትና ለመገንባት እንዲያስችልም ራሱን የቻለ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተቋቁሟል።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ኃላፊ ዶክተር ሂያብ ገብረፃድቅ እንዳሉት፥ እንጦጦ በተፈጥሮ ሃብቶች የተከበበ ሥፍራ እንደመሆኑ መጠን ማዕከሉ ሲገነባ ሀገር በቀል ዛፎችን እና እጽዋትን በመትከል ተፈጥሯዊ ውበትን የተላበሰ እንዲሆን ይደረጋል።
በያዝነው አመት የሚጀመረው የማዕከሉ ግንባታ ከአምስት አመታት በኋላ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።( ኤፍቢሲ)