የፌዴራል ሥርዓቱ በነፃነት ተዘዋውሮ የመስራት መብትን አጎናፅፏል-አስተያየት

ኢትዮጵያ የምትከተለው የፌድራል ሥርዓት ለዜጎች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውረው የመስራት መብትን ያጎናፀፈ መሆኑን በመቀሌ ከተማ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ሰዎች ገለፁ፡፡

በመቀሌ ከተማ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ዜጎች ለዋልታ እንደገለፁት የፌዴራል ሥርዓቱ ያጎናፀፋቸውን መብት በመጠቀም ኑሮዋቸውንና ሥራቸውን ከትውልድ ቦታቸው ውጭ አድርገዋል፡፡

በሂሳብ ሥራ የተሰማሩት ወይዘሮ ዘቢት አየለ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚመጡ ዜጎች ቅድሚያ እየተሰጠ በመቀሌ ከተማ ሥራ የሚጀምሩበት ሁኔታ እንደሚመቻች ይገልፃሉ፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭት መፈጠሩን ከማህበረሰብ ሚዲያዎች መስማታቸውን የሚጠቁሙት ወይዘሮ ዘቢት ችግሮች ካሉ በሠላማዊ መንገድ መጠየቅና ተገቢው ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ የመከባበርና የመቻቻል ባህልን አጠናክሮ መጓዝም ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ነው ያሰመሩበት፡፡

አቶ አብነት አስራት በመቀሌ ከተማ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ በፈለጉት አካባቢ ተዘዋውሮ እንዲሰራ ያጎናፀፈውን መብት በተግባር ማየቱን ራሱን በማሳያነት ያቀርባል፡፡ ሥራውን በሠላማዊ መንገድ እያከናወነ እንደሚገኝም ነው የሚናገረው፡፡

ለሁሉም ነገር ሠላም ዋናው መሰረት በመሆኑ ለሠላምና መረጋጋት ዘብ መቆም እንደሚገባ አቶ አብነት ተናግረዋል፡፡

በመቀሌ ከተማ ለ33 ዓመት በሹፌርነት ሙያ ያገለገሉት አቶ አበባው ቸኮልና ለሰባት ዓመት በሹፌርነት ሙያ የቆየው ወጣት ችሎት አስፋው የሌሎቹን ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ በተለይም ሁሉም ለሠላምና መረጋጋት ቅድሚያ ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንዳለበት ያገነዛባሉ፡፡

በመቀሌ ቆይታቸው ሥራቸውን በሠላም ከማከናወን ውጭ ያጋጠማቸው አንዳችም ችግር የለም ብለዋል፡፡ ከሌላ አካባቢ ለሚመጣ ዜጋ ቅድሚያ የመስጠት ጥሩ አቀባበል በከተማዋ መኖሩንም ሳይጠቁሙ አላለፈም፡፡

አስተያየት ሰጭዎቹ እንዳሉት የኢትዮጵያውያን አኩሪ ባህል የሆነው ተከባብሮ፣ተደጋግፎና ተቻችሎ የመኖር ዕሴት በደንብ ሊጠናር ይገባል፡፡ ግጭትን ማውገዝና መከላከልም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በሠላማዊ መንገድ ጥያቄዎችን ማንሳትና ተገቢውን ምለሽ መስጠትም በሚመለከታቸው አካላት ሊታሰብበት ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አንቀፅ 32 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ‹‹ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በህጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት፤ እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት መብት አለው…›› ይላል፡፡