የአማራ ክልል ሰላም ወደ ነበረበት ተመልሷል-መንግስት

የአማራ ክልል ሰላምና መረጋጋት ወደ ነበረበት መመለሱን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ዛሬ በተለይ ለዋልታ እንዳስታወቁት፤ በክልሉ አንዳንድ አከባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው ሁከት ረግቦ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ሰላም ሰፍኗል፡፡

በክልሉ የተከበረው ብዙ ህዝብ የሚሰበሰብበት የዳመራ በዓል  ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ መከበሩ አንዱ መሳያ መሆኑን አንስተዋል ፡፡

ሰላም በመፈጠሩም የክልሉ የገጠርም የከተማም ህብረሰተሰብ ወደ ተለመደ ዕለት ተዕለት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ መመለሱን አረጋግጠዋል ፡፡

የአማራ ክልል ወክለው ወደ መቐለ የተጓዙ የአገር ሽማግሌዎች በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል አቶ ንጉሱ ፤፤

የትግራይ ህዝብና የአማራ ህዝብ መቼውም ቢሆን በማንኛውም ደረጃ አይጋጭም ያሉት አቶ ንጉሱ ፤ነገር ግን የክልላቸውና ብሎም የሀገሪቱን ሰላም እንዲናጋ፤ ሰላም እንደጠፋና ብጥብጥ እንዲነግስ የሚያስቡ ወገኖች ግጭት ሊፈጥሩባቸው የሚችሉ ክስተቶች አንዱ ብሄርን መሰረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ስለሆነም አልፎ አልፎ ይህ በአንዳንድ አከባቢዎች ምልክቶችና ችግሮች በመግጠሙ ህብረተሰቡም መንግስትም ይህንን ክስተት በሰፊው አውግዞታል ነው ያሉት፡፡

በመጀመሪያ ደረጃም የአማራ ክልል ህዝብና መንግስት የማይወክል ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሰላምን በማረጋገጥ አኳያ ህብረተሰቡ በጋራ መመካከርና በየደረጃው በሃይማኖትም በሽምግልናም  ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል ፡፡

ከሁሉም በላይ ግን ህብረተሰቡ በመጀመሪያ ያነሳቸውን ችግሮች መፍታት ስለሆነ ችግሮችን የሚፈቱበት አግባብ ደግሞ ሰላማዊ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን አስገንዝበዋል ፡፡

የማይፈቱ ችግሮች ደግሞ በሰለጠነ ሁኔታ መፍታት ፤ባጭር ጊዜ የማይፈቱትን ደግሞ ከህብረተሰቡ ጋር ተግባብቶ ተመካክሮ በሚፈቱበት ጊዜ መግባባት ላይ መድረስ መሆኑን አብራርተዋል ፡፡

መፍታት የማይችሉትን ደግሞ ከህብረተሰቡ ጋራ ግልጽነት ይዞ ህዝብን በወቅቱ ማሳወቅ ይገባል ብለዋል፡፡

ማንም ሰው የሃሳብ ልዩነት ሊኖሮው የማይችለው ሰላምን በመጠበቅ ጉዳይ ላይ መግባባት እና ሁሉም በየድርሻው እንዲወጣ የሚችልበት ሁኔታ መፍጠር ይሰራል ነው ያሉት ፡፡

ምክንያቱም ህብረተሰቡ ሰላሙን ጠብቆ መቀጠል የሚችለው  በዋናነት ሰላምና አገር ሲኖር ብቻ ነው ሲሉም ያስገነዝባሉ ኃላፊው ፡፡

ከውጭም የሚደረግብንን ጫና፣ የአገራችንን ውድቀት የሚሹ የአገራችን ቀና ማለት የማይፈልጉ አካላትን መታገል የሚቻለው ሰላማችንን በንቃት ስንጠብቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ህብረተሰቡ በማንኛውም አግባብ ልዩነቱንና ጥያቄውን ሰላማዊ በሆነ መልኩ እያቀረበ ሰላማዊ የሆነ ትግል በማድረግ ችግሮች መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡

በዚህ ላይ የጋራ መግባባት ደርሶ ችግሮችን በሰላም ለመፍታትና ስለ ሰላም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መምከር መወያየትና መፍትሄ ማስቀመጥ ያለበት መሆኑን ተገንዝቦ ሁሉም በሚገኝበት ቦታና ኃላፊነት የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል ፡፡