ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢሬቻ በዓል ላይ የዜጎች ሕይወት በማለፉ ሃዘናቸውን ገለጹ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኢሬቻ በዓል ሥነ ስርዓት ላይ ትናንት በተፈጠረው ሁከት የዜጎች ሕይወት በመጥፋቱ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማምሻውን ባስተላለፉት መልዕክት የኢሬቻ በዓል ለኦሮሞ ሕዝብ የሰላም፣ የመረጋጋት፣ የመቻቻልና መልካም ምኞት መግለጫው ነው ።

በዓሉን በተረጋጋ መንፈስ በመልካም ሁኔታ እያከበረ ባለበት ወቅት በጥፋት ኃይሎች በተከሰተው ሁከት የ52 ሰዎች ህይወት በመጥፋቱ ጥልቅ ኃዘን እንደተሰማቸው አስታውቀዋል፤ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ተመኝተዋል።

የበዓሉ ስፍራ ገደላማ መሆን፣ በመገፋፋትና መረጋገጥ ምክንያት ዜጎች ህይወታቸው ያሳለፈ ሁከት መፈጠሩ ”አሳዛኝና አስከፊ ሂደት ነው” ሲሉ ድርጊቱን ኮንነውታል።

የመቻቻልና የአንድነት ምልክት በሆነው የኢሬቻ በዓል ስነ ስርዓት ላይ የዚህ ዓይነቱ ድርጊት ሊከሰት የማይገባው እንደነበር ጠቁመዋል።  

የኦሮሞ ሕዝብ ወደ ሆራ ቢሸፍቱ በለሊት በመሄድ በዓሉን በሰላም ማክበር መጀመሩን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አባገዳዎች ይህን በዓል በአንድነት፣ በሰላምና በመረጋጋት አምላካቸውን ለማመስገን መርሃግብሩን እየመሩት እንደነበርም ጠቁዋል።

ሆኖም በጥፋት ኃይሎች በተከሰተው ሁከት ሕይወት አልፏል።

ድርጊቱ ከኦሮሞ ህዝብ ተግባር ያፈነገጠና ክብሩን የሚነካ መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ይህን አይነቱን ድርጊት በምሬት መቃወምና መንግስት አጥፊዎቹን ወደ ህግ እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል።ለዚህም መላው የኦሮሞ ሕዝብ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

ሁከቱ ሲፈጠር መንግስት ለማረጋጋት ከፍተኛ ጥረት ያደረገበትና የጥይት ድምጽ ያልተሰማበት መሆኑን ጠቁመው፤ የጸጥታ ሃይሉ ሁከቱን በሰላማዊ መንገድ ለማረጋጋት ባደረገው ጥረት አመስግነዋል።

መንግስት ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በመሆን በዓሉን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ሰፊ ዝግጅት አድርጓል።

የኤፌዴሪ መንግስት የጀመረውን የለውጥ፣ የልማትና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውዋል -/ኢዜአ\ ።