በኢሬቻ በዓል ላይ ጉዳት ከደረሰባቸው 100 ዜጎች 97ቱ ከሆስፒታል ወጥተዋል

በኢሬቻ በዓል በተፈጠረ ሁከት በመረጋገጥ እና መታፈን ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር 55 ደርሷል።

የቢሾፍቱ ሆስፒታል ዛሬ በሰጠው መግለጫ በትናንትናው እለት በአደጋው ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ዜጎችን 54 አስከሬን እንደተቀበለ አሳውቋል። 

በዛሬው እለትም አደጋው በደረሰበት ሆራ አርሰዲ በሚገኘው ገደላማ ስፍራ ውስጥ አንድ አስከሬን መረከቡን የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ባይሳ ተናግረዋል። 

ስራ አስኪያጁ ሁሉም አስከሬኖች እስከ ዛሬ እኩለ ቀን ድረስ ለቤተሰቦቻቸው ተሰጥተው ወደየመጡበት አካባቢ መላካቸውንም አንስተዋል። 

በአደጋው 100 ሰዎች ላይ ቀላል፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሷል። 

በአጠቃላይ የመቁሰል አደጋ ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል 97ቱ የህክምና አገልግሎት አግኝተውና ህክምናቸውን ጨርሰው ከሆስፒታል ወጥተዋል። 

በአሁኑ ወቅት ሁለት ታካሚዎች በቢሾፍቱ ሆስፒታል፤ ሌላ አንድ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ታካሚም ወደ ሌላ የህክምና ተቋም ሪፈር ተፅፎለት በመታከም ላይ እንደሚገኝ ዋና ስራ አሰኪያጁ በመግለጫው አንስተዋል። 

የሟቾቹን የሞት ምክንያት አስመልክቶ ዝርዝር መግለጫ የሰጡት የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አስድ አህመድ፥ ሟቾቹ በመረጋገጥ፣ በመታፈንና እርስ በርስ በተፈጠረ መተፋፈግ ጉዳት ደርሶባቸው ህይወታቸውን እንዳጡ በምርመራ አረጋግጠናል ብለዋል። 

ከሟቾቹም ሆነ ከቁስለኞቹ መካከል አንድም ሰው በጦር አልያም በሌላ መሳሪያ ጉዳት የደረሰበት አልተገኘም።

የሞቱ ዋና ምክንያትም መረጋገጥ እና መታፈን ብቻ ነው ብለዋል ዶክተር አሰድ።

ከሟቾቹ መካከል አስሩ ሴቶች መሆናቸውንም ሆስፒታሉ አስታውቋል።

የቢሾፍቱ ከተማም የሀዘን ድባብ ብትላበስም በተለመደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች-(ኤፍ.ቢ.ሲ) ።