ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በኢሬቻ በዓል ላይ የሰው ህይወት በመጥፋቱ ሐዘናቸውን ገለጹ

ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በኦሮሚያ ክልል በኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ ጸረ ሰላም ኃይሎች በፈጠሩት ግርግር በደረሰው የህይወት መጥፋት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል ።

ጥልቅ ሐዘናቸውን የገለጹት የአፋር፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የደቡብ፣የጋምቤላና የሀረሪ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታትና የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ህዝብና መንግስት ናቸው  ።

ጸረ ሰላም ኃይሎች የኦሮሞ ህዝብ መለያና እሴት የሆነውን የእሬቻ በዓል የፖለቲካ አቌማቸውን ለማራመድ ሲሉ በፈጠሩት ግርግር ለ55 ሰዎች ህይወት መጥፋትና ለ100 ሰዎች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መዳረጋቸው እንዳሳዘናቸው አመልክተዋል።

የክልሉ መንግስታትና አስተዳደሮቹ ለቤተሰቦቻቸው እና ለኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል ።

የእሬቻ በዓል በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል  ።