በእሬቻ በዓል በተፈጠረው ሁከት ጎዳት ለደረሰባቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ክልሉ አስታወቀ

የኦሮሚያ  ብሔራዊ ክልል  መንግሥት  የታላቁ እሬቻ  በዓል በሚከበርበት በቢሸፍቱ ሆራ አርሴዲ  በተፈጠረው ሁከት ህይወታቸውን ላጡና ጉዳት ለደረሰባቸውና ተጎጂ ቤተሰቦች አስፈላጊውን  ድጋፍ  እንደሚያደርግ አስታወቀ ።

የክልሉ  መንግሥት ምክትል ፕሬዚደንት አቶ እሸቱ ደሴ በጨፌ ኦሮሚያ  በሠጡት መግለጫ  እንደገለጹት የክልሉ መንግሥት በተከሰተው ሁከትና ግርግር ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖችናቤተሰቦች ድጋፍ እንደሚያደርግና ከጎናቸው እንደሚቆም አመልክቷል።

ባለፈው እሁድ  በእሬቻ  በዓል  ላይ  በፀረ ሰላሙ  ኃይል  በተፈጠሩት ሁከትና ግርግር የተነሳ  የሰው ህይወት  መጥፋቱን   የገለጹት አቶ እሸቱ    የተፈጠረው  ሁከትና ግርግር መንግሥት ከአየርና ከምድር በከፈተው ተኩስ እንደሆነ  በማስመሰል  በማህበራዊ  ሚዲያዎች  ሃሰተኛ ፕሮፖጋንዳ  እየተነዛ  ይገኛል ብለዋል ።

ህብረተሰቡ  በተለያዩ  ማህበራዊ  ሚዲያዎችን በሚሠራጩ  ሃሰተኛ  መረጃዎች ሳይደናገር  የተለመደውን  በብሔርና ሃይማኖት ልዩነቶችን  የማቻቻል  ባህሉን  በማጠናከር   ለዘላቂ ሰላም  መከበር   የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አቶ  እሸቱ ጥሪ  አቅርበዋል ።

በተጨማሪም  ይህ  ሁከት  የተከሰተው   የእሬቻ  በዓል  መገለጫ የሆነው  የገዳ ሥርዓት በአለም አቀፍ ደረጃ  ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት በሚደረግበት  ወቅት  መሆኑንና  የኦሮሞ   ባህል እንዳያድግ  የተፈጸመ  ስውር ሴራ መሆኑን  የጠቆሙት  አቶ እሸቱ   ለወደፊቱም ባህሉን በቅርስነት ለማስመዝገብ   የሚደረገው ጥረት  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል ።

የእሬቻ በዓል   ለዘመናት የኦሮሞ ህዝብ ክረምትን አልፎ  ወደ በጋ  በሚሸጋገርበት ወቅት ለፈጣሪ  ምስጋና  የሚያቀርብበት  በዓል ነው ።