ፖሊስ በአዲስ አበባ ፀረ ሰላም ኃይሎች ከሚያናፍሱት ወሬ ውጪ ሁሉም እንቅስቃሴ ሰላማዊ ነው አለ

 በአዲስ አበባ ፀረ ሰላም ኃይሎች ከሚያናፍሱት ወሬ ውጪ ከተማዋ በሰላማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ትገኛለችሲል ፖሊስ ገለፀ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ጀነራል አሰፋ አብዩ እንደተናገሩት፥ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ውስን ቦታዎች ላይ ትናንት እና ዛሬ በኢሬቻ በዓል ላይ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ ሁከት ለማስፋፋት ጥረት ተደርጓል።

በዚህ ሙከራም ከውጭ ኃይሎች ትዕዛዝ በመቀበል ለሁከት የሚሰሩ እና የሚፈጠሩ ግርግሮችን በመጠቀም በተለይም ፋብሪካዎችካባቢ ለዘረፋ የተቀላቀሉ ሰዎች መሳተፋቸውን ነው ያመለከቱት።

በሂደቱ ውስጥ ያለምንም መረጃ እንዲሁ የተቀላቀሉ እንዳሉም ተናግረዋል።

ነገር ግን በእነዚህ ቦታዎች የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ከፀጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን ህገወጥ እንቅስቃሴውን መቆጣጠር መቻሉን ነው ዋና ጀነራል አሰፋ አብዩ የተናገሩት።

በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ከአዲስ አበባም ሆነ በዙሪያዋ የሚገኙ ከተሞች ከሚገኙበት ነባራዊ ሁኔታ የራቀ የበሬ ወለደ ወሬ መነዛቱን አንስተዋል።

ይህም የመዲናዋ ነዋሪ በዓመፅና ሁከት ተግባር እንዲሳተፍ የተሠራጨ መሆኑን ህብረተሰቡ ተረድቶ መደበኛ እንቅስቃሴውን እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የፀጥታ ኃይሉም ከህዝቡ ጋር በመሆን ለየትኛውም የአመፅና ሁከት ተግባር ተመጣጣኝ እርምጃ እንደሚወስድ ነው ያስታወቁት።(ኤፍቢሲ)