መንግስት ለሕዝብ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጥሪ አቀረበ

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ መንግስት የሕዝብ ጥያቄዎችን በማድመጥ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ አቀረበ።

የጉባዔው መሪዎችና የበላይ ጠባቂዎች ወቅታዊውን የአገሪቷ ሁኔታ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

መሪዎቹ በመግለጫቸው በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ለማርገብም ሆነ ሃሳብን ለመግለጽ በሚደረግ ጥረት ሁሉም ወገን ከምንም በላይ ለሰው ሕይወት ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም በኢሬቻ በዓል ላይ በተከሰተው ግርግርና ሁከት በዜጎች ላይ በደረሰው የሕይወት መጥፋትና የአካል መጉደል የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን በመግለጽ ለተጎጂ ቤተሰቦች፣ ዘመድ ወዳጆችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን ተመኝተዋል።

የጉባዔው ጠቅላይ ፀሃፊ መጋቢ ዘርይሁን ደጉ እንደተናገሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ጠፍቷል፣ የአካልና የመንፈስ ጉዳት ደርሷል፣ ንብረትም ወድሟል።

የጉባዔው መሪዎችና የበላይ ጠባቂዎች በአገሪቷ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከጠቅላይ ሚንስትሩና ከሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር የሕዝቡ ጥያቄ ተደምጦ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲያገኝ መወያየታቸውንም አስታውሰዋል።

"ከጊዜ ወደ ጊዜ የአገሪቷ ሠላም እየደፈረሰ መምጣት የሃይማኖት መሪዎችን በእጅጉ አሳስቧል" ነው ያሉት መጋቢ ዘርይሁን።

የተቀሰቀሰውን ግጭት ወደ ሠላም የመለወጥ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት መንግስት በአርቆ አስተዋይነት ተገቢውን ሁሉ እንዲያደርግ ጠይቀው ሕዝቡም አገራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ አሳስበዋል።

የተለያየ ዕምነት ተከታይ የሆኑ ዜጎችም ለሠላምና ለአገር ልማት በመቆም ጥያቄዎቻቸውን በአግባቡ ማቅረብ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

በግጭቱ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡና ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻችም ጠይቋል።

ጉባኤው የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ መገናኛ ብዙሃን፣ ማህበራዊ ድረ ገጾችና ግለሰቦች ሕዝብን ወደ ጥላቻ፣ ግጭትና ሁከት ብሎም ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት ወደ ማጥፋት የሚመራ መረጃ ከማሠራጨት እንዲታቀቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።( ኢዜአ)