የወጣቶች፣ የሲቪል ሰርቪሱንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መንግሥት ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደሚወስድ የኢፌዲሪ ፕረዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አስታወቁ ።
ፕሬዚዳንት ሙላቱ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳስታወቁት ፤መንግስት በሁሉም የአገሪቱ ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ በ10 ቢሊዮን ብር በጀት ሊቋቋም ነው።
በምክርቤቶቹ በሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመን መንግሥት ዘንድሮ ለወጣቶች የኃብትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት መስጠቱን አመልክተዋል፡፡
በዚሁም መሰረት ለወጣቶች የሥራ መነሻ የሚሆን በሚቋቋመው የተንቀሳቃሽ ፈንድ ወደ ተግባር እንደሚገባ አስታውቀዋል ።
ከዚህ ጎን ለጎን የሥራ ፈጠራ የሚያተኩርባቸው መስኮች ተለይተውና ከወጣቶች ጋር ተመክሮባቸው ወደ ትግበራ እንደሚገባ አመልክተዋል።
"መንግሥት ከፈንዱ አጠቃቀምና የፕሮጀክቶች ትግበራ ተያይዞ ከወረዳ አመራርና ከወጣቶች ጋር በመመካከር የዓቅም ግንባታ ድጋፍ በመስጠት የሚያስፈጽም መሆኑን አብራርተዋል ።
የወጣቶች ፍትሃዊ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎትና ጥያቄዎች ያሏቸው በመሆኑ ጥያቄዎችን አስተሳስሮ መፍታት እንደሚገባ ፕሬዝዳንቱ አስምረውበታል።
በተለይም የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ቀድሞ መፍታት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ በመሆኑ በትኩረት እንደሚሰራበት ጠቁመዋል ።
የሲቪል ሰርቪሱን ጨምሮ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችሉ ተጨማሪ ዕርምጃዎች መንግሥት እንደሚወስድ አስታውቀዋል። የሲቪል ሰርቪሱን ጨምሮ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መንግሥት ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ገልጸዋል ።
የአገሪቱ ሲቪል ሰርቪስ ከአገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ጋር ተመጋጋቢ በሆነ የደረጃ ተጠቃሚ እየሆነ እንዲሄድ በየወቅቱ የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ያደረገ የደመወዝ ማስተካካያ እንደሚደረግም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል ሲል ዋልታ ዘግቧል ።