የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በዛሬው ዕለት ሠጠው መግለጫ ከመስከረም 22 እስከ 27 2008 ዓም በክልሉ በጥቂት ወረዳዎች ተፈጥሮ የነበረው ሁከት መረጋጋቱን አስታውቋል ።
ባለፈው ሳምንት በክልሉ የምስራቅ ሸዋ ዞን ሰባት ወረዳዎች ፣ በምዕራብ አርሲ ዞን አምስት ወረዳዎች ፣ በምስራቅ አርሲ ዞን አራት ወረዳዎች ፣ በምዕራብ ጉጂ ዞን ሦስት ወረዳዎችና የሰበታ ከተማ ሁከት የተፈጠረባቸው የክልሉ አካባቢዎች መሆናቸው ተመልክቷል ።
የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማ ለጋጤጠኞች እንዳብራሩት ባለፈው ሳምንት የፀረ ሰላም ኃይሎች በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በፈጠሩት ሁከቶች በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል ።
የፀረ-ሰላም ኃይሎቹ በተለይም በኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ ትኩረት በማድረግ 68 የሚደርሱ የኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ። በአጠቃላይ 12 የውጭና 56 የአገር ውስጥ የኢንቨስትመንት ኩባንያዎች ላይ ጥቃቱ ደርሷል ።
ጥቃት ከደረሰባቸው ኩባንያዎች መካከል ሁለቱ ሙሉ ለሙሉ ውድመት የደረሰባቸው ሲሆን አራቱ ለዝርፊያና የተቀሩት 62 የሚሆኑት ደግሞ በከፊል የመሰባበርና የእሳት ቃጠሎ አደጋ ሰለባ ሆነዋል ።
የአበባ እርሻዎች ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ድርጅቶች፣ የጨርቃ ጨርቅ ፣ ፕላስቲክና የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የጥቃቱ ኢላማ መሆናቸውን አቶ ፈቀዱ አመልክተዋል ።
ከፋብሪካዎቹ ውጭም የተለያዩ መንግሥታዊና የግል ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱን አቶ ፍቃዱ አያይዘው ገልጸዋል ።
መንግሥት ከህብረተሰቡ ጋር ያደረገው ውይይት በክልሉ የፀረሰላም ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋልና መረጋጋትን ለመፍጠር እየተደረገ ላለው እንቅስቃሴ እገዛ ማድረጉ ተጠቁሟል ።