በሻኪሶ ከተማ 47 ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ

ከሻኪሶ ከተማ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ ሲጓጓዙ የነበሩ በርካታ ህገወጥ የጦር መሳሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ ።

በከተማው በአቦስቶ ፍተሻ ጣቢያ ከተያዙት የጦር መሳሪያዎች ውስጥ 8 ክላሾች፣ 7 ሽጉጦችና 32 ኋላ ቀር የጦር መሳሪይዎች እንደሚገኙበት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አህመድ አላዲን ጀማል ገልጸዋል ።

በተለየ መልኩ ለህገወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውር ታቅዶ በተዘጋጀ አይሱዙ ተሽከርካሪ ከሻኪሶ ተጭነው ሀዋሳ ከዚያም አዲስ አበባ እንዲገቡ የታቀደ ቢሆንም በፍተሻ ጣቢያው መያዛቸውን አብራርተዋል ።

ህገወጥ ጦር መሳሪያዎቹ በሀገሪቱ ሁከት እና ግርግር ለመፍጠር ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደነበርም ነው ምክትል ኮሚሽነሩ ያስረዱት።

የጦር መሳሪያዎቹ በፀረ ሰላም ሀይሎች እጅ ቢገቡ በዜጎች ሰላም እና ደህንነት ላይ የሚያደርሰውን አደጋ ከባድ ይሆን እንደነበር አመልክተዋል ፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ በቀጣይ የሀገርን ሰላም ለማወክ የሚታትሩ አፍራሽ ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የተጠናከረ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል ።

ህብረተሰቡም  ፀረ ሰላም ሀይሎች እንቅስቃሴ ለመግታት ፖሊስ የሚያደርገውን ጥረት እንዲያግዝ መጠየቃቸውን የዘገበው ኢቢሲ ነው ።